የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ አዲስ ኃላፊ የሥራ ርክክብ አደረጉ
መስከረም 28/2019 ዓ/ም – ሀላባ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሆነው አዲስ የተሾሙት አቶ ሳሙኤል መንገሻ ከቀድሞው የቢሮው ኃላፊ አቶ አክመል አህመዲን ጋር የሥራ ርክክብ አደረጉ።
በሥራ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ አቶ አክመል አህመዲን በኃላፊነት ባገለገሉበት ወቅት ከጎናቸው ለነበሩ የማኔጅመንት አባላትና ለመላው የቢሮው ሠራተኞች ላደረጉላቸው የሥራ ትብብርና ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ የቢሮው ምክትል ኃላፊዎች፣ የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት፣ ክልሉ ከተመሠረተ ጀምሮ በፍትህ ዘርፍ ለተከናወኑ ሥራዎችና አቶ አክመል አህመዲን በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት ላሳዩት የአመራር ብቃት አድናቆታቸውንና ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ተሳታፊዎቹ በተጨማሪም ከአዲሱ የቢሮው ኃላፊ ጋር በመቀናጀት ቀደም ሲል የተጀመሩ ሥራዎችን በተሻለ ትኩረት በማስቀጠል ወደ ተግባራዊ ውጤት ለማሸጋገር በትጋት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
አዲሱ የቢሮው ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ በበኩላቸው፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲጠናከርና የሕዝብን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ የፍትህ አገልግሎት እንዲሰጥ ከየደረጃው ካሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የቢሮውን የቀደመ አፈጻጸም በማስቀጠልና በማሻሻል፣ ተቋሙ የተሰጠውን ሕጋዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ ሁሉንም አካላት አሳትፈው እንደሚሠሩም አቶ ሳሙኤል አስገንዝበዋል።
በሥራ ርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ የቢሮው ምክትል ኃላፊዎች፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ የማኔጅመንት አባላትና የቢሮው ሠራተኞች ተገኝተዋል።
በመጨረሻም ለቀድሞው የቢሮው ኃላፊ አቶ አክመል አህመዲን ጋቢ የማልበስና መልካም ምኞት የመግለጽ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል።
ፍቅርተ ዘለቀ
የቢሮው መ/ኮሚኒኬሽን