Skip to main content

የ 2018 ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ
ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ። 

መጋቢት:-15 /2018 ዓ.ም 

የክልሉ ፍትህ ቢሮ በምርጫ ህግ ፤ በጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በመከላከል ዙሪያ ያተኮረ የምክክር መድረክ በቡታጀራ ከተማ  አካሂዷል። 

በመርሀ ግብሩም ከዞንና ከልዩ ወረዳ ፍርድ ቤቶች የተውጣጡ ዳኞች፣ ከፍትሕ መምሪያዎች የተወከሉ ዓቃቢያነ ሕግ፣ ከፖሊስ መምሪያዎች የተገኙ መርማሪ ፖሊሶች እና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል። 

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ፍትህ ቢሮ ም/ኃላፊ እና የህግ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም በድሩ እንደገለፁት፣ የፊታችን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው 7ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች የሥልጣን ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን፣ የፍትሕ ተቋማት ብስለትና ዝግጁነት የሚፈተንበት  ወቅት ነው። 

ምርጫ የነፃነት መግለጫ መሆን እንጂ የሁከት ምንጭ መሆን እንደማይገባም አጠናክረው  ገልጸዋል። 

በዚህም መሠረት ዳኞች ገለልተኛና ፈጣን ውሳኔ መስጠት፣ ዓቃቢያነ ሕግ የሕግና የሕዝብ ጥበቃን ማረጋገጥ፣ መርማሪ ፖሊሶችም ጥሰቶችን በፕሮፌሽናል መንገድ መመርመር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል። 

በመድረኩ ከተነሱ አንዱ ዋና ጉዳይ ደግሞ በቴክኖሎጂ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ መረጃዎች በምርጫ ሂደት ላይ የሚያሳድሩት አደጋ ነበር። 

እነዚህ ድርጊቶች የሕዝብ እምነትን ሊያበላሹና ሰላማዊ ምርጫን ሊያደናቅፉ እንደሚችሉ ተገልጿል። 

በመሆኑም የፍትሕ አካላት የነጻ አስተያየት መብትን እያከበሩ፣ ነገር ግን ሀገርና ሰላምን የሚያናጋ የጥላቻ ንግግርና የሐሰት መረጃ ስርጭትን በሕግ መቆጣጠር እንዳለባቸው ተነግሯል፣ የሲቪክ ማኅበራትም ሕዝቡን በማንቃት፣ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ በማስተማርና ሂደቱን በቅርብ በመከታተል ትልቅ ሚና መጫወት እንዳላቸው ተገልጿል። 

በመድረኩም በቢሮው ዐቃቤ ህግ በአቶ ጢሞትዮስ ዋርጎ እና በአቶ ደረጀ ደስታ የመወያያ ሰነዶች ቀርበው ተሳታፈዎች ጥልቅ ውይይት አድርገውበታል 

በመጨረሻም መድረኩም ተሳታፊዎች ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ሕጋዊ አሰራሮችን የሚያጠናከሩበት እና ለምርጫው ስኬት በአንድነት ለመስራት ቃል የሚገቡበት መሆን እንደሚገባው ተገልጿል።

Image
የ 2018 ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።