Skip to main content

በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መከላከል እና ምላሽ አሰጣጥ ዙርያ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጠ።
*****
ሚያዝያ  20 / 2018 ዓ.ም ሀላባ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ድርጊቱ ሲፈፀም ፈጣንና ፍትሃዊ ምላሽ ለመስጠት ያለመ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በወራቤ ከተማ ተሰጠ።

በሥልጠናው  በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በተለይ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ-እድሜ ጋብቻን ለመከላከል እና ተፈጽሞ ሲገኝ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የሚሰሩ ዐቃቤያነ-ህጎች፣ መርማሪ ፖሊሶች እና የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር በማድረግ መድረኩን ያስጀመሩት የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ አክመል አህመዲን ሲሆኑ በንግግራቸውም 
ቢሮው ለሴቶችና ህፃናት መብትና ደህንነት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከክልል እስከ ታችኛው የፍትህ መዋቅር ድረስ የተደራጀ የሥራ  ክፍል እንዲደራጅ በማድረግ ባለሙያዎችን በመመደብ የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ኃላፊው አያይዘው በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ የጥቃት ድርጊቶቹ በብዛት የሚፈፀሙባቸውን አካባቢዎች በመለየት ከUNICEF ጋር በመተባበር የበጀት፣ የቁሳቁስ እና የሥልጠና ድጋፎችን እየሰጠ ቢሆንም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተጨማሪ ጥረት እንደ ሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ሥልጠናው በተለይ በመጋቢት 24/2018 ዓ.ም የፀደቀው አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ህግ (አዋጅ ቁጥር 1410/2018) ላይ ትኩረት በመስጠት ተሳታፊዎች ዲጅታል ማስረጃዎችን እና ዘመናዊ የምርመራ ስልቶችን በተግባር እንዲጠቀሙ  አሳስበዋል።

ኃላፊው በማከልም ተሳታፊዎች የጉዳዩን አሳሳቢነትና ውስብስብነት በጥልቀት እንዲገነዘቡ እና በሥልጠናው የሚገኙ ክህሎቶችን በተግባር በማዋል በመረጃ አያያዝና በአላላክ ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም 
የሴቶችና ህፃናትን መብት የሚጎዱ አካላትን በህግ አግባብ ተጠያቂ በማድረግ አስተማሪ ውሳኔዎች እንዲሰጡ እና ሁለንተናዊ ጥበቃ እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል።

በመቀጠልም ለሥልጠናው የተዘጋጀው ሰነድ በቢሮው  ዐቃቤ ህግ በአቶ ጢሞትዮስ ዋርጎ ቀርቦ ተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎ  አድርገውበታል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎች ባነሷቸው ሀሳቦች ላይ የቢሮው የሴ/ህ ልዩ የም/ ክስ ጉ/ ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ አፈወርቅ ደሚሴ እና በአቶ ጢሞትዮስ ዋርጎ ምላሽና አስተያየት የተሰጠ ሲሆን፤ የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ሁሉም አካል የሚጠበቅበትን ተግባር በመከወንና ተቀናጅቶ ለመስራት በመዘጋጀት  ፍትሕ እንዲረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ በማቅረብ የማጠቃለያ ሀሳቦች ተሰጥተው  መድረኩ ተጠናቋል።

የቢሮው መ/ኮሚኒኬሽን

Image
በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መከላከል እና ምላሽ አሰጣጥ ዙርያ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጠ።