Skip to main content

በሰው መነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመግታት የህግ ማዕቀፍ ማጠናከር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ
ሀላባ፣ ሰኔ 11/2018 ዓ.ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ HOPE FOR JUSTICE ከተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ኢ-መደበኛ ፍልሰትን፣ በሰው መነገድን እና ህገ-ወጥ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 እና ደንብ ቁጥር 32/2017 አስመልክቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የHOPE FOR JUSTICE የፕሮግራሞች ዳይሬክተር አቶ ፈይሳ ተፈራ ሲሆኑ፣ የመክፈቻ ንግግሩን ያቀረቡት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህግ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም በድሩ ናቸው።
አቶ አብርሃም በንግግራቸው እንደገለጹት፣ በሰው መነገድና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች በዜጎች ህይወት፣ ደህንነትና ሰብዓዊ መብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ችግሩን በህግ፣ በቅንጅት እና በህዝብ ተሳትፎ ለመከላከል የተጠናከረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም፣ አዋጁና ደንቡ የሰው መነገድን፣ ህገ-ወጥ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን እና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርን ለመከላከል እንዲሁም የፍልሰት አስተዳደርን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የህዝብ አደረጃጀቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና የሙያ ማህበራት በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያግዝ የትብብር ሥርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል።
በክልሉ በተለይም በሀድያ፣ በከምባታ ጠምባሮ፣ በጉራጌ፣ በምዕራብ ጉራጌ፣ በስልጤ እና በሀላባ ዞኖች የሚስተዋሉ በሰው መነገድና ህገ-ወጥ ፍልሰት ችግሮችን ለመቀነስ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የክትትል እና የቅንጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።
በመቀጠል ለውይይት የተዘጋጀውን ሰነድ ያቀረቡት የቢሮው የፍልሰት ትብብር ጥምረት አስተባባሪ አቶ ታደሰ መንድሙ ሲሆኑ፣ በአዋጁና በደንቡ ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ ዐቃቤ ህጎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ችግሩን ለመከላከል የራሳቸውን ድርሻ በተጠናከረ መልኩ ለመወጣት ቁርጠኝነታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ህብረተሰቡም ከህገ-ወጥ የፍልሰት መንገዶች በመራቅ ህጋዊ አሰራሮችን መከተል እንደሚኖርበት ተገልጿል፡ 
በመጨረሻም የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ እና የህግ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሀም በድሩ እና የHop for justce የፕሮግራሞች ዳይሬክተር አቶ ፈይሳ ተፈራ በማጠቃለያ ንግግራቸው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አመላክተዋል።

Image
በሰው መነገድና  ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመግታት የህግ ማዕቀፍ ማጠናከር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ