ፍትህ ቢሮ በቀድሞው የደቡብ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት አስፈጻሚ ተቋማት መካከል አንዱ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ከለውጡ ማግስት (2010 ዓ/ም) ወዲህ በክልሉ የሚገኙ ህዝቦች በየወቅቱ ከሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ውስጥ ጎላ ያለ ስፍራ ይዞ የነበረው በየደረጃው የነበረው የመዋቅራዊ አደረጃጀት ጥያቄ መነሻነት በ2012 ዓ.ም በተካሄደው የህዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት የሲዳማ ክልል እና በ2013 በጀት ዓመት በተካሄደ የህዝበ ውሳኔ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከነባሩ ክልል በመውጣት በክልልነት መደራጀታቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህም በመቀጠል በቀሪው የደቡብ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት በነበሩ መዋቅሮች ይነሱ የነበሩ የአደረጃጀትና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት መንግሥት በ2015 በጀት ዓመት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተካሄደው የህዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት ከደቡብ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት በመውጣት በክልልነት ለመደራጀት መወስኑን ተከትሎ ቀሪው መዋቅር ነባሩ የደቡብ ክልል የነበሩ ህጎችን፣ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን በማሻሻል እንደገና እንዲደራጅ በመወሰኑ ከነሐሴ 12-13 ዓ.ም በወልቂጤ ከተማ በተካሄደው የክልሉ መስራች ጠቅላላ ጉባኤ የክልሉን ህገ-መንግሥት በማፅደቅ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በይፋ ተመስርቷል፡፡
በአዲስ መልክ የተደራጀው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 199/2015 ላይ ከተዘረዘሩ አስፈጻሚ አካላት መካከል አንዱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ነው፡፡
በመሆኑም ቢሮው በክልሉ መንግስት የተጣለበት ተግባርና ኃላፊነት መወጣት በሚያስችለው መልኩ በተለያዩ የዘርፍ አደረጃጀቶችና የሥራ ክፍሎች በማደራጀት ለተገልጋዩ ሕብረተሰብ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና ተደራሽ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን ዕርካታ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡