በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች የክረምት ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ
(ሆሳዕና፣ ሀምሌ 4/2017)፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከመላው ኢትዮጵያ ለተወጣጡ የክረምት ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች በሆሳዕና ከተማ አቀባበል ተደርጓል።
"በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል ለ4ኛ ጊዜ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ የወሰን ተሻጋሪ የክረምት ወራት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አገልግሎት በክልሉ መካሄድ ጀምሯል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ ወጣቶቹን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉት ወቅት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዓለማ፤ ወጣቶችንና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችን በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታትና የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ባህል ሆኖ እንዲጎለብት የማድረግ ሚናን መጨወት መሆኑን ተናግረዋል።
በጎነት ውስጥ ፍቅር፣ ሰላም፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ የሌሎች ሰዎችንና የተቸገሩ ወገኖችን፣ ምንም ምላሽ ሳይጠብቁ ችግር በመፍታት የመንፈስና የአዕምሮ እርካታ የማግኘት ክንዋኔ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሰዎች ከሰብዓዊነት አመለካከት ተነስተው፣ ለማህበረሰብ ልማትና ለአካባቢ ደህንነት፣ በነፃ ልምዳቸውን፣ ገንዘባቸውን ፣ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና በጎ አመለካከታቸውን በመልካም ተግባር ላይ የሚያውሉበት መሳሪያ ነው ሲሉም አቶ ጌታቸው ገልፀዋል።
የክልሉ መንግስት ባለፉት ዓመታት ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊ የበርካታ አረጋውያንና፣ የወላጅ አልባ ህፃናትን ችግር የፈታና የብዙዎችን ህይወት የቀየረ ተግባር በ14ቱም የስምሪት መስኮች ተከናውኗል ብለዋል።
እንደ ክልል የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕቅድ ከ4 ሚሊዮን 258 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍልን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ከ2 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበትና በሂደቱም ከ2 ቢሊየን 42 ሚሊየን ብር በላይ ከመንግስትና ከህብረተሰብ የሚወጣውን ወጪበሁሉም የስማሪት መስኮች ለማዳን መታቀዱንም አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።
ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመጡት ወጣቶች የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ፣የቢሮው ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ሃላፊ አቶ አቢቲ ኢንሴቦ፣የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አመራሮች፣የክልሉ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት ደገፈ ደበሮ፣የሆሳዕና ከተማ ወጣት አደረጃጀት ተወካዮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ወጣቶቹ በቆይታቸው የችግኝ ተከላ ፤ አከባቢን የማፅዳት፤ ደም የመለገስ፤ ለችግር የተጋለጡ ህሙማን/አረጋውያን /ህፃናትና ሴቶችን የመንከባከብ ስራ ለይ እንዲሁም የገጠር ኮሪደር ልማት ስረዎችን ምልከታ እንደሚያደርጉም ተጠቁሟል።
ምንጭ ፦ የክልሉ መ/ኮ
