Skip to main content

የሴቶችና ህፃናትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ያስፋልጋል -  ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች እና ባለሙያዎች በክልሉ በሴቶችና ህጻናት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን ምልከታ አድርገዋል።

(ሆሳዕና፦ ሀምሌ 6/2017) ፣ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮችና ባለሙያዎች ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን በሴቶችና ህፃናት ዘርፍ የተሰሩ ተግባራትን ነው ምልከታ ያደረገው።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር  ሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን እንደተናገሩት ከድህነት ለመላቀቅ በሴቶች ህብረት መደራጀት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው ብለዋል።

ሴቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ  ናቸው ያሉት ወ/ሮ ሂክማ የሴቶችንና ህፃናትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

በሴቶችና ህፃናት ዘርፍ መስራት ሀገር ላይ መስራት በመሆኑ የኢትዮጵያን ሴቶችንና ህፃናትን  በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የበለጠ መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሴቶችና ህፃናት ዙሪያ የተለያዩ መመሪያዎች እና ደንቦችን በመወጣት ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እራሳቸውን እንዲጠብቁና በልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎች እየሰራ ነው ብለዋል።

ሁሉም ሴቶች ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመውጣት የተጀመረውን ስራዎች በማስቀጠል የመረዳዳት ባህልን ማጉላት ያስፈልጋል ብለው በዞኑ በተሰሩ ስራዎች መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘቢባ መሀመድ ናስር እንደገለፁት የሴቶችንና ህፃናትን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከምን ጊዜም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ  እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሴቶች ልማት ህብረት ውጤታማነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት  መሆናቸውን በተግባር ለማየት ተችሏል ብለዋል።

የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ የሁሉም አካላት ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቅ ነው ብለው ሴቶችን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማላቀቅ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

በጉራጌ ዞን ተግባሩ ከተከናወኑ መዋቅሮች ውስጥ አንዱ በሆነው እዣ ወረዳ ወርት ቀበሌ በሴቶች ልማት ህብረት የተሰሩ ስራዎች የተመለከተ ሲሆን በወልቂጤ  ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሳተላይት ካምፓስ እና በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል  ህፃናት ማቆያ ማዕከላት ተይቷል።

የልማት ህብረት ሴቶች እንደተናገሩት በሴቶች ልማት ህብረት በመደራጀት ተጠቃሚ ስለመሆናቸው በመጥቀስ  በዶሮና በፍየል እርባታ፣በእደ ጥበብ ስራዎች፣ በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ  ተግባራት በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በልማት ህብረቱ ስለ ትምህርት፣ ጤና፣ ንፅህና አጠባበቅ፣ ወሊድ፣ በህፃናት አስተዳደግ፣  ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መከላከል ፣ በሌማት ትሩፋት እና ሌሎች ተግባራት ውጤቶች እየመጡ መሆኑ  ተጠቁሟል።
ምንጭ :- የክልሉ መ/ኮ

Image
የሴቶችና ህፃናትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ያስፋልጋል -  ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን