Skip to main content

በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

ሆሳዕና፣ሐምሌ 7/2017)በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ላይ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደመሰረተ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2016/2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን ከተለያዩ የዘርፉ ተጠሪዎች ጋር እየገመገመ ባለበት መድረክ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ተወካይ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት ከ116 ግለሰቦች ላይ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሞባይል ባንኪግ በማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ላይ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደተመሰረተባቸውገልጸዋል።

ተከሳሾቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከሌሎች የግል ባንኮች የሚደውሉ በማስመሰል እንዲሁም የኮምፒውተር ሥርዓትን በመጠቀም አሳሳች መረጃዎችን በማሰራጨት ወንጀሉን እንደፈጸሙ ፖሊስ መግለፁን አንስተዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የቀረበው ክስ እንደሚያብራራው፣ ተጠርጣሪዎቹ ማንነታቸውን በመሰወርና ሀሰተኛ ሰነዶችን እና መታወቂያዎችን በማዘጋጀት እና በመጠቀም የተበዳዮችን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበው ክስ በዋናነት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ እና የኮምፒዩተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 958/2008ን እንዲሁም የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003ን የተላለፉ መሆናቸውን ይገልጻል።

ለወንጀል ድርጊቱ ማስፈጸሚያነት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ በርካታ የባንክ አካውንቶች፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ሲም ካርዶች እና ኮምፒውተሮች እንደተያዙ ተገልጿል፡፡

ጉዳዩን ለማጣራትም ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Image
በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ