በዱራሜ ከተማ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የሚገነባው የአካል ጉዳተኞች ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ግንባታ የቦታ ርክክብ ተደረገ።
በተለያዩ ምክንያቶች ኮንትራቱ ተቋርጦ የነበረው የአካል ጉዳተኞች ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በአዲስ መልክ ጨረታ በማውጣት ለአሸናፊው ተቋራጭ የሳይት ርክብክብ መደረጉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል ። ግንባታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑም ተመልክቷል።
የቢሮው ምክትልና የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ሠርካለም ሣሙኤል ተቋርጦ የነበረው የአካል ጉዳተኞች ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በየደረጃው ከሚመመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ርብርብ ፕሮጀክቱ በድጋሚ እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል ተጀምሮ በተፈለገው ፍጥነት መሰራት ባለመቻሉ በአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ መልክ ጨረታ ወጥቶ በ60 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በጀት ጨረታውን ላሸነፈ ኮንትራክተር በማስተላለፍ በአጭር ጊዜ እንዲሠራም ጠንካራ ድጋፍና ክትትል ይደረጋልም ብለዋል።
የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትልና አሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ በይዳ ሙንዲኖ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞችና አረጋውያንን ያማከለ ተቋማት አለመበራከት ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው ማዕከሉ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ማለታቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያሳያል ።
