Skip to main content

በክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሴቶችና ህፃናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተመላከተ

(ሆሳዕና፣ ሀምሌ 10/2017)፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ እና የክልሉ የሴቶች አደረጃጀት የጋራ ፎረም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በማረቆ ልዩ ወረዳ አካሂደዋል።

በመርሃ ግብሩ የችግኝ ተከላ በቆሼ አጠቃላይ 2ተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የአቅመ ደካማ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ በኢላላ ጅረኖ ቀበሌና ለቀበሌው የሴቶች የልማት ህብረት ድጋፍ የተበረከተ ሲሆን፣ የሴቶችን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታም ተደርጓል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሐመድናስር፣ በክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሴቶችና ህፃናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

የሴቶች የልማት ህብረት ሁሉ አቀፍ ተግባራትን ማሳኪያ መሆኑን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊዋ፣ ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሴቶች የልማት ህብረትን ይበልጥ እያጠናከሩ መሄድ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በማረቆ ልዩ ወረዳ ዲዳ ሀሊቦ ቀበሌ እየተከናወኑ የሚገኙ የሴቶች የልማት ስራዎች አበራታች መሆኑን ያነሱት የቢሮ ኃላፊዋ የሴቶች ልማት ህብረቱ በተደራጀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ መመልከት መቻሉን አብራርተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሴቶችና ህፃናት የጀርባ አጥንት መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ዘቢባ፣ ህብረቱ የአቅመ ደካማ እናቶች ቤትን ባጭር ጊዜ ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚገባውም አመላክተዋል።

የማረቆ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አማሮ በበኩላቸው በአካባቢው የነበረውን የፀጥታ ችግር ከክልሉ የሠላምና ፀጥታ ጋር በመቀናጀት በተከናወኑ ተግባራት በአባቢው ሰላምን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

በአካባቢው ሠላም መረጋገጡ በልዩ ወረዳው የልማት ስራዎችን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ዋና አስተዳዳሪው አንስተው የሴቶችን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በቅንጅትና በትብብር መንፈስ መስራት እንደሚገባም አቶ ጀማል አመላክተዋል።

የማረቆ ልዩ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ቀመሪያ ከድር፣ የሴቶችንና ህፃናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ወረዳው በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በማረቆ ልዩ ወረዳ የኢላላ ጅረኖ ቀበሌ ነዋሪ እማ ወራ ዳንጉሌ ወጀጎ የመኖሪያ ቤታቸው በክረምት ወራት ለኑሮ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተደረገላቸው ትብብር መደሰታቸውን በመግለፅ፣ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።

ምንጭ :- የክልሉ መ/ ኮ

Image
በክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሴቶችና ህፃናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተመላከተ