Skip to main content

መንግስት ለዘላቂ ሰላም እና ለሀገራዊ አንድነት በትኩረት እየሰራ  ይገኛል-ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ሆሳዕና ፤ሐምሌ 10/2017፦መንግስት ለዘላቂ ሰላም እና ለሀገራዊ አንድነት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ እና ለዚህም አስተማማኝ መሰረት መጣሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ለኢዜአ አመራሮች እና ሰራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፥ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት መሰረት የመጣል፣ገለልተኛ ተቋማትን የመገንባት እና ለሌብነት የማይመች የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር ላይ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም መንግስት ለዘላቂ ሰላም እና ለሀገራዊ አንድነት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ለዚህም አስተማማኝ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።

መንግስት ነጠላ ትርክት ለሀገር የማይበጅ መሆኑን በውል በመረዳት የጋራ ትርክት እሳቤን በመከተል እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምን በመተግበር ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ማድረጉን አመልክተዋል።

በቀጣይም፥ ምርታማነትን ማሳደግ፣የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን የበለጠ ማጎልበት፣ገቢን ማሳደግ፣የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል እና የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማጠናቀቅ የመንግስት የትኩረት መስኮች ናቸው ብለዋል ።ዘገባው የኢዜአ ነው።

Image
መንግስት ለዘላቂ ሰላም እና ለሀገራዊ አንድነት በትኩረት እየሰራ  ይገኛል-ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)