Skip to main content

ክልሉን ከአፈር ማዳበሪያ እዳ ነፃ ለማድረግ የክልሉ መንግስት የወሰደው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።

(ሆሳዕና ፣ሐምሌ 10/2017) ፣የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የግብርና ሚኒስቴር በቅንጅት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ2017/18 ምርት ዘመን የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት ላይ የተደረገ ሱፐርቪዥን ግብረ መልስ ለክልሉ ግብርና ቢሮ ሰጥቷል።

በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የቡድኑ መሪ የተከበሩ ሰለሞን ላሌ ብልሹ አሰራርን በመታገል ክልሉን ከአፈር ማዳበሪያ እዳ ነፃ ለማድረግ የክልሉ መንግስት የወሰደው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ምርጥ ዘር ስርጭት ላይ መሻሻሎች መኖሩን ተናግረው እርሶ አደሩ አማራጭ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እንዲጠቀም መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአርሶአደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት በማጥናት አርሶአደሩ የሀገር ውስጥ ምርት በስፋት እንዲጠቀም መሰራት ይገባልም ብለዋል።

ክልሉ የባህር ዛፍን በማንሳት በፍራፍሬና ሌሎች ሰብሎች ለመተካት የጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሶፊያ ካሳ እንደገለፁት እንደሀገር በቂ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት መኖሩን ተናግረዋል።

የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት አገልግሎት አሰጣጡን በዲጅታል በማዘመን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቤኔዘር በቀለ የግብርና ኤክስቴንሽን ስራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመስክ ምልከታው የታዩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ጉድለቶችን ፈጥኖ በማረም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።

ግብረ ሃይሉ በክልሉ የ2017/18 ምርት ዘመን የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና ስርጭትን ተዘዋውረው ምልከታ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ምንጭ :- የክልሉ መ/ኮ

Image
ክልሉን ከአፈር ማዳበሪያ እዳ ነፃ ለማድረግ የክልሉ መንግስት የወሰደው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።