የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅን አጸደቀ
(ሆሳዕና፣ሐምሌ 10/2017)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅን አፅድቋል።
አዋጁ ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ ግብር ነፃ የተደረገውን የብር መጠን 600 ከነበረበት ወደ 2ሺህ ከፍ አድርጓል፤ 35 በመቶ የግብር ክፍያ መጠን መነሻው ከ14 ሺህ ብር በላይ በሆነ ደሞዝ ላይ ይተገበራል።
ከገቢ ግብር ነፃ የተደረገው 2ሺህ ብር አጠቃላይ ከሀገሪቱ ገቢ 38 ነጥብ 44 ቢልዮን ብር እንደሚያሳጣ ተገልጿል።
የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ ፤ ማሻሸያ አዋጁ የሀገሪቱን የገቢ መሰብሰብ አቅም ለማሳደግ የተቀመጠውን ግብ ታሳቢ በማድረግና ለልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የገቢ ግብር አዋጁ ሳይሻሻል የቆየ በመሆኑና አሁን የተቀመጠው ምጣኔም መንግሥት ያገኝ የነበረውን ገቢ በመተው መሆኑን ገልፀዋል።
ማሻሸያ አዋጁ አትራፊ ኩባንያዎች መክፈል ያለባቸውን ግብር እንዲከፍሉ በሌላ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ለኪሳራ የተዳረጉ ድርጅቶችን በዓመታት ውስጥ ማካካስ እንዲችሉ የፈቀደና ሁለቱንም መንገድ በማጣጣም የተዘጋጀ ነው።
አዋጁ ከግብር ከፋዩ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚመልስ፣ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ማጭበርበርን የሚገታ መሆኑን አብራርተዋል።
በግብር ሥርዓት ውስጥ ከተመዘገቡት ግብር ከፋዮች መካከል ግብር የሚከፍሉት ከ63 በመቶ የማይሻገሩት መሆናቸውን አንስተው፣ የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ይህንን ክፍተት በመሙላት ፍትሐዊ የግብር ሥርዓትን ያረጋግጣል።
የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጁ ተቃጣሪ የመንግስት ሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን በማንሳት በድጋሚ እንዲታይ የምክር ቤቱ አባለት ጠይቀዋል።
ምክር ቤቱ ማሻሻያ አዋጅን በ12 ድምጽ ተአቅቦና በ5 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
ኢፕድ
