በአባል እና በአመራራችን የጋራ ጥረት ዓመቱን ስኬታማ ያደረጉ ድሎችን መጎናፀፋችንን ገምግመናል፡- አቶ አደም ፋራህ
(ሆሳዕና ፣ሐምሌ 10/2017)
በአባል እና በአመራራችን የጋራ ጥረት ዓመቱን ስኬታማ ያደረጉ ድሎችን መጎናፀፋችንን ገምግመናል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ቀናት በድሬደዋ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የብልፅግና ፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተጠናቋል፡፡
በመድረኩ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት በጥልቅ መገምገማቸውን የገለጹት አቶ አደም፣ኢትዮጵያን ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሻገር የሚያስችል አቅምን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳበርን እንደመጣን፣ በአባል እና በአመራራችን የጋራ ጥረት ዓመቱን ስኬታማ ያደረጉ ድሎችን መጎናፀፋችንን ገምግመናል ነው ያሉት።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ዓመታዊ ሪፖርትንና በፓርቲ መሪነት የተካሄደውን ሀገር አቀፍ የሱፐርቪዥን መርሀ ግብር አፈፀፀምን በመገምገም፣ ለፓርቲው ተቋማዊ አሰራር ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የአደረጃጀት እና የአሰራር መመሪያ እንዲሁም በሀብት አስተዳደር መመሪያዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት መካሄዱን ጠቁመዋል።
ከተካሄደው ውይይት ጎን ለጎን የፓርቲው አመራሮች እና አባላት "በመትከል የማንሰራራት" ግብን በመያዝም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር ችግኞችን ተክለዋል።
አቶ አደም ፋራህ "በድሬዳዋ ከተማ በክቡር የፓርቲያችን ፕሬዚዳንት የመደመር መፅሀፍ ገቢ የተሰራውን የእመርታ ቤተመፅሀፍት፣ የድሬዳዋ ከተማ የኮሪደር ልማትን፣ የድሬ ስቲል የብረታ ብረት ፋብሪካ እና አማ የምግብ ዘይት ማቀነባበሪያ ድርጅትን ብሎም በሕዝብ፣ በመንግስት እና በግል ባለሀብቶች ቅንጅት የተሰሩ ሌሎች የልማት ስራዎችን ጎብኝተናል" ብለዋል።
በቆይታቸው ከፓርቲ ስራዎች ግምገማ ባሻገር በ2017 በጀት ዓመት በፓርቲና መንግስት ቅንጅት በንቅናቄ ተግባራዊ ሲደረጉ የነበሩ ከተረጂነት የመላቀቅ፣ የኑሮ ውድነትን የማቃለል እና የክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራ አፈፃፀምን በመመልከት ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጣቸውን ጠቅሰዋል።
አቶ አደም መርሐ ግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረጉ የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤትን እና ሌሎች አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እንዲሁም እርምት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ በማድረግ የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ግብን ለማሳካት እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የጀመርነውን ጉዞ አጠናክረን እንደምንቀጥል ለመግለፅ እወዳለሁ ሲሉም አክለዋል።
