በከተሞች እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ የመንግስት ፖሊሲዎች፣ስትራቴጂዎች እና ፕሮግራሞች በተገቢው መንገድ ተፈጻሚ ስለመሆናቸው አመላካች ነው - ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ
(ሆሳዕና፣ሐምሌ 14/2017)፣የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቡታጅራ ከተማ የልማት ፕሮደክቶች ምልከታ አድርገዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ እንደገለጹት የመስክ ምልከታው አብይ ዓላማ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን የታቀዱ ተግባራት ከወረቀት ሪፖርት ባለፈ ምን ያህል ተፈጻሚ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው።
በክልሉ የመስክ ምልከታ በተደረገባቸው ከተሞች የመንግስት ፖሊሲዎች፣ስትራቴጂዎች እና ፕሮግራሞች በተገቢው መንገድ ተፈጻሚ ስለመሆናቸው የምክር ቤት አባላት ተገንዝበዋል ሲሉም ዋና አፈ ጉባኤዋ አስረድተዋል።
እንደ ሀገር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጡ ኢኒሼቲቮችን በማሳደግ በክልሉ ተግባራዊ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ዋና አፈ ጉባኤዋ በአብነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ አመራሩ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ያለውን ጸጋ በመጠቀምና የህብረተሰብ ተሳትፎን በማጎልበት ማልማት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ለውጥ እንደሚመጣ የተናገሩት ዋና አፈ ጉባኤዋ በተለይ የከተማ ኮሪደር እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በከተሞች የሚካሄደው የልማት ስራ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲካሄድ ከማስቻል ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን ዋና አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል።
የክልሉ ህዝብ የመንግስትን የልማት ግብ ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ የላቀ አቅም እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
በመስክ ምልከታው በዚህ አመት ግንባታቸው እየተካሔደ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት በላቀ ቁርጠኝነት በፍጥነት ወደ ተግባር መግባታቸውን ዋና አፈ ጉባኤዋ ጠቁመዋል።
ክልሉ ተመስርቶ ስራ ሲጀምር በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ነበር ያሉት አፈ ጉባኤዋ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በጽናት በማለፍ የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ እያካሔደ መሆኑን ተናግረዋል ።
በክልሉ የማህበረሰቡን ችግር መፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ኢኒሼቲቮች ተፈጻሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ ለአብነት የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ የተገነቡ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የገለጹት ዋና አፈ ጉባኤዋ በተለይ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል።
በከተማው የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የተቋቋሙት የሰንበት ገበያዎች በአምራቹና ሸማቹ መካከል ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
በመስክ ምልከታው የምክር ቤት አባላት ክልሉ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኑን ስለመገንዘባቸው ዋና አፈ ጉባኤው አብራርተዋል።
የምክር ቤት አባላት በከሰዓት ውሎ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የልማት ስራዎች ምልከታ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።
