Skip to main content

የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር አሰራርን ለማሻሻል በትኩረት መስራት ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና፣ሐምሌ 17/2017)የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ እየተካሔደ ነው

ምክር ቤቱ በከሰዓት ውሎው የክልሉን ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ (ዶ/ር)በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር አሰራርን ለማሻሻል በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

ተከታታይነት ያለው የድጋፍና ክትትል ስራ በማከናወን ተገቢ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በተስተዋሉ የአሰራር ጥሰቶች ፖለቲካዊ፣አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ተችሏል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

የኦዲት  ግኝቶች ላይ ዘላቂነት ባለው መንገድ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በኦዲት ግኝት ላይ በተስተዋሉ ጉዳዮች ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር እንደ ጉዳዩ ሁኔታ ህጋዊ፣አስተዳደራዊ አሊያም ፖለቲካዊ ውሳኔ በሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ ኦዲት የተደረጉ ተቋማት በአጭር ጊዜ ማስተካከያ እንዲያደርጉ መስራት ተገቢ ነው ብለዋል።

በኦዲት ግኝት ላይ የሚስተዋሉ ጉዳዮችን በመለየት አሰራርን ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት የጋራ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም  ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።

‎የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ፈዲላ አደም ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የኦዲት ሪፖርት እንደገለጹት በክልል መንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ የተከናወኑ የገቢ፣ የፋይናንስና ህጋዊ ኦዲት፣የክዋኔና አካባቢ ኦዲት የልዩ ኦዲት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

የኦዲት ስራው እንደተጠናቀቀ ከሚመለከታቸው የኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ጋር በኦዲት ግኝቶች ላይ ውይይት መደረጉን ዋና ኦዲተሯ አመላክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ኦዲት ከተደረጉ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የገቢ አሰባሰባቸው፣የበጀት አጠቃቀማቸው፣የሂሳብ አያያዛቸው እና የንብረት አስተዳደራቸው ከወጡ ህጎች አንጻር መፈተሽ ተገቢ ነው ብለዋል።

ይህን ተከትሎም ነቀፌታ የሌለበት አስተያየት የተሰጣቸው 8፣ነቀፌታ ያለበት አስተያየት የተሰጣቸው 43፣ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት 13፣እንዲሁም አስተያየት መስጠት ያልተቻለበት  አንድ መስሪያ ቤት መኖሩን ነው ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ፈዲላ የተናገሩት።

መስሪያ ቤቱ ተገቢውን የኦዲት ስራ እንዲያከናውን የትብብር እና የቅንጅት ስራ ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።

በኦዲት ግኝት ላይ መታረም ያለባቸው አሰራሮች ውጤታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ እና አስፈጻሚ አካላትሊያግዘን ይገባል ሲሉም ዋና ኦዲተሯ አብራርተዋል።

ምንጭ ፦ የክልሉ መ/ኮ

Image
የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር አሰራርን ለማሻሻል በትኩረት መስራት ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)