Skip to main content

ለሕዳሴው ግድብ ድጋፋችንን እናጠናክራለን - የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት

ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 21/2017)፦ የአብሮነት መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ግድቡ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ልምድ የተቀሰመበትና ለሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት የሚጥል መሆኑን የምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል።  

‎በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል ‎በምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ግዛቸው ዋሌሬ የግድቡ ግንባታ ሀገራዊ ልማትን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።

በተለይ ‎ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዳይሳካ ሲደረጉ የነበሩ ጫናዎችን በመቋቋም በቁርጠኝነትና በአይበገሬነት መሰራቱ ለትውልዱም በፈተና ውስጥ ለሀገር እድገት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።

ከክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ጌታሁን ነጋሽ በበኩላቸው፣ የግድቡ ግንባታ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ገንዘብ በማዋጣትና ህብረተሰቡን በማስተባበር የዜግነት ሀላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል።

‎ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ አሌይካ ሽኩር በበኩላቸው ግድቡ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ መድረሱ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን ማልማት እንደምትችል በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

‎በቀጣይም ለሀገራዊ እንድነትና ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ላይ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

‎ከብታቸውን ሽጠው ቦንድ በመግዛት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግም ሌላው የምክር ቤቱ አባል ‎አርሶ አደር ሃጅ ገራድ ተታ ሙዜ ናቸው።

በ‎ቀጣይም የተጀመረው ሀገራዊ እድገት ከዚህም በላይ እንዲፋጠን የልማት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Image
ለሕዳሴው ግድብ ድጋፋችንን እናጠናክራለን - የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት