Skip to main content

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ስራ እንደሚከናወን ተገለጸ።

(ሆሳዕና፣ ሀምሌ 21/ 2017)፣ በማረቆ ልዩ ወረዳ ቆሼ ከተማ የወጣቶች  የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የክልሉ ወጣቶች ክንፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ወጣት አብዱ ድንቁ በክልሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት እና ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ስራ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚከናወን ተናግሯል።

የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ14 ልዩ ልዩ የትኩረት መስኮች የሚከናወን ሲሆን፣ 5 ሺህ ዩኒት ደም ለመለገስ እና 12 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ይሰራል ብሏል።

በልዩ ትኩረት የኢትዮ ኮደርስና ፋይዳ መታወቂያ ንቅናቄ በማካሄድ 500 ሺህ ወጣቶች ግንዛቤ የሚፈጠር እና 28 ሺህ ያህል ወጣቶች ስልጠናውን ሙሉ ለሙሉ አጠናቀው ሰርተፊኬት እንደሚያገኙ ወጣት አብዱ ገልጿል።

የማረቆ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አማሮ፣ አካባቢው ከነበረበት የፀጥታ ችግር እንዲላቀቅ የክልሉ መንግስት፣ የፀጥታ አካላት፣ ማህበረሰቡና ወጣቶች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል። ወጣቱ የተረጋገጠውን ሰላም እንዲጠብቅ፣ ለልማትና ብልጽግና እንዲተጋ አሳስበው፣ በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ ለተሳተፉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

በኩኖ አሌመና ቀበሌ የአቅመ ደካማ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ስራ። የአከባቢው የግብርና ስራ እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ ተደርጓል።  በተመሳሳይ በቆሼ ከተማ የደም ልገሳ እና የችግኝ ተከላ ተከናውኗል።

ምንጭ፦ የክልሉ መ/ ኮ

Image
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ስራ እንደሚከናወን ተገለጸ።