በዓለም አቀፍ የውል ድርድርና ዝግጅት ዙሪያ ያተኮረ በአይነቱ ልዩ የሆነ ስልጠና ተጀመረ
**********
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ከአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ /TDB Group/ ጋር በመተባበር በአለም አቀፍ ውል ዝግጅትና ድርድር ሂደቶች ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስራ ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል፡፡
ከፌዴራል እና ከክልል ተቋማት የተወከሉ በውል ሂደት ለሚሳተፉ ከ56 በላይ የህግ ባለሙያዎች ከሐምሌ 21 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በሚሰጠው ተግባር ተኮር ስልጠና ላይ በመስኩ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አለምአቀፍ እና የውጭና ሀገር ውስጥ አሰልጣኞች የሚሳተፉበት ሲሆ፤ ውሎችን በሚገባ በመደራደርና የተቋማትን ጥቅም በተሟላ ሁኔታ የሚያስጠብቁ ስምምነቶችን በማዘጋጀት የህዝብና የመንግስት ጥቅም ለማስጠበቅ አጋዥ የሆነና ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ባለሙያዎች የተሳተፉበት በአይነቱ ልዩ የሆነ የአለምአቀፍ የውል ድርድርና ዝግጅት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ /TDB Group/ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የ/TDB Group/ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አድማሱ ታደሰ፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ መስራች ሀገር መሆኗን አስታውሰው፣ የ/TDB Group/ በተለያዩ ሀገራት በግብርና እንዲሁም በኢንደስትሪ ዘርፎች ከዚህ በተጨማሪ በቢዝነስ ውልና ድርድሮች ላይ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በመሳተፍ አለምአቀፍ የውል ዝግጅትና ድርድሮች ላይ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አንፃር አለምአቀፍ የቢዝነስ ውል ድርድርና ዝግጅት ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎችን ለማብቃት ታሳቢ ተደርጎ ስልጠና መዘጋጀቱ በዘርፉ ላይ ተጨማሪ አቅምን መፍጠር የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለተከታታየ አምስት ቀናት የሚቆየውና ትኩረቱን አለም አቀፍ የቢዝነስ ውል ዝግጅትና ድርድሮች ላይ ያደረገ የአቅም ግንባታ የስልጠና መድረክን የመክፈቻ ንግግር በማድረግ በይፋ ያስጀመሩት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትህ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሐን{ዶ/ር} ስልጠናውን በማዘጋጀት የተባበሩ አጋር አካላትን አመስግነው የአቅም ግንባታ ስልጠናው የፌደራል ተቋማትና ክልሎች የውል ስራዎቻቸውን በእውቀት የተደገፈ እንዲሆን በማስቻል በሀገራችን በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የህዝብና የመንግስት ተቋማት በጀትና ሃብቶች ይበልጥ እንዲጠበቁ እንደሚያስችል አልፀዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ክልሎችን ጨምሮ በሁሉም ደረጃ የሚደረገው የአቅም ግንባታ ስራ የሀገርና ተቋምን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ውሎች እንዲመሩ በማድረግ የህዝብ በጀት እንዲጠበቅና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱን ለመደገፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለው እንደገለጹት የውል ድንጋጌዎችን አስመልክቶ አለመግባባት ከመከሰታቸው በፊት በተለይ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በቢሊዮን ብር የሚገመቱ የፕሮጀክት ውሎች ድርድርና ዝግጅቶች በሚገባው የጥንቃቄ ደረጃና በትኩረት መመራት እንዲችል መሰል የተግባር ስልጠናዎች አጋዥ መሆናቸውን በመጥቀስ ስልጠናው በዘርፉ የሚስተዋለውን የሙያ አቅም ክፍተቶችን ለመሙላትና አሁናዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሙንና አለም አቀፍ ከባቢ ሁኔታው እድገት የሚፈልገውን ዝግጁነት በማጎልበት የህዝብን ጥቅም በተሟላ መልኩ ያማከለ ምላሽ ለመስጠት አጋዥ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
በዚህ ስልጠና የሚገኘው ክህሎት በቀጣይ በሚኖሩ ስራዎች ላይ አተገባበሩ አፅንኦት ተሰጥቶት ክትትል የሚደረግበት መሆኑና ከመሰል የልማት አጋሮች ጋር በመቀናጀት ተከታታይ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱ ተመላክቷል፡፡ በአለም አቀፍ ውል ዝግጅትና ድርድር ሂደት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስራ ስልጠና ተዘጋጅቶ እንዲሰጥ በተለያየ ደረጃ አስተዋፅኦ ያበረከቱት Trade and development bank group(TDB Group) ፣ African Legal Support Facility (ALSF), New Perimeter እና DLA PIPER ሲሆኑ እስከ ሀምሌ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ መድረክ አለምአቀፍ የቢዝነስ ውል ዝግጅትና ድርድር ቴክኒኮች ዙሪያ ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥ ለመረዳት ተችሏል፡፡
