የህዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ህዝብ ጋር የሚያደርጉት ቀጥተኛ ውይይት መንግስትና ህዝብን በማቀራረብ ረገድ የላቀ ሚና አላቸው አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ
(ሐምሌ 29/2017)የክልል እና የፌደራል የፓርላማ አባላት በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዙር የህዝብ ውክልና ስራ ማከናወን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሔደ ነው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ እንደገለጹት የሀገሪቱ ህገ-መንግስት ፓርላሜንታዊ ስርዓትን የሚከተል በመሆኑ ህግ አውጪው፣ህግ አስፈጻሚው እና ህግ ተርጓሚው ተለይተው ሚናቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።
የህግ አውጪው ዋነኛ ተግባር ከሆኑት መካከል የውክልና ስራ ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ ይህን ተከትሎም የምርጫ አካባቢ ተግባራትን ሲያከናውን የህዝብ ፍላጎትና ጥቅምን በጠበቀና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ህዝብ ጋር የሚያደርጉት ቀጥተኛ ውይይት መንግስትና ህዝብን በማቀራረብ ረገድ የላቀ ሚና እንዳላቸው ዋና አፈ ጉባኤዋ በንግግራቸው አመላክተዋል።
የመረጃ ክፍተትን መቀነስና ግልጽነትን በማሳደግ ረገድ ተመራጮች ከህዝብ ጋር በሚኖራቸው ውይይት የመንግስትን ፖሊሲዎች እቅዶች እና አፈጻጸሞች በቀጥታ ለህዝቡ ያስረዳሉ ሲሉም ዋና አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል።
ይህን ተከትሎም ህዝቡ በቂ መረጃ ሲያገኝ ስለ መንግስት ውሳኔዎች እና ምክንያት ሲያውቅ በመንግስት ላይ ያለው እምነት እንደሚጨምር ጠቁመዋል።
በየጊዜው በሚከናወን የህዝብ ውክልና ስራ በመንግስት አሰራር ላይ ግልጽነት መፍጠር እንደሚያስችልም ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ አስረድተዋል።
የውክልና ስራው ሲጠናከር ተመራጮች የህዝቡን ትክክለኛ ፍላጎቶች፣ችግሮች እና ቅሬታዎችን መረዳት ያስችላቸዋል ሲሉም ዋና አፈ ጉባኤዋ ጠቅሰዋል።
በመንግስት ፖሊሲዎች ውስጥ የህዝቡን ድምጽ ለማሳካት ይረዳል ያሉት አፈ ጉባኤዋ ከህዝቡ የሚገኙ ግብአቶች እና አስተያየቶች መንግስት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች እና ህጎች የህዝቡን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ መፍትሄ ያስገኛሉ ብለዋል።
የተመራጭ መራጭ ቀጥታ ውይይት የመረጃ ክፍተትን በመቀነስ ግልጽነትን ያሳድጋል ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ የህዝብን ድምጽ በማድመጥ የውሳኔ አሰጣጥን ያሻሽላል ብለዋል።
በሌላ በኩል ተጠያቂነት እና መልካም አስተዳደርን በማጎልበት የጋራ የባለቤትነት ስሜት ይፈጥራል ያሉት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን አመኔታ ያሳድጋልበማለት አብራርተዋል።
ግጭትን በመከላከል ሰላምን በማስፈን ረገድ የሚኖረው ሚና የላቀ ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ የመራጭ ተመራጭ ውይይት የዴሞክራሲ ስርዓትን የሚያጠናክር፣ህዝብን ማዕከል ያደረገ ልማትን የሚያስቀጥል እና ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም አፈ ጉባኤዋ በንግግራቸው አብራርተዋል።
በመድረኩ የክልል እና የፌደራል የፓርላማ አባላት የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምንጭ፦ የክልሉ መ/ኮ
