ለግብርናው ዘርፍ ግቦች ስኬት በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ክትትልና ድጋፍ ቁልፍ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ።
( ሀምሌ 5/2017)፣የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ከክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር የግብ ስምምነት ተፈራርሟል።
በግብርናው ዘርፍ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀመጡ ግቦችን ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ተከታታይ ክትትልና ድጋፎች ቁልፍ አስተዋጽኦ አላቸው ሲሉ በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ተናግረዋል ።
አቶ ኡስማን የክልሉ ግብርና ቢሮ ከክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በ2018 በጀት አመት የሴክተር እቅድ የግብ ስምምነት ሲፈራረም እንዳሉት ምክር ቤቶች የዘርፉ ወጤቶችና ግቦች መሳካታቸውን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና አላቸው። የተቀመጡ ቁልፍ ግቦች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን የምናረጋግጥበት ነው ሲሉም አክለዋል።
የምክር ቤቶች ድጋፍና ክትትል የተቋም ግምባታን ለማሳለጥና ዘላቂ የአሰራር መሰረት ለመጣል ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል ።
በክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ልክነሽ ስርገማ በበኩላቸው ምክር ቤቱ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን አፈጻጸም በመደገፍና በመከታተል የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ሴክተሮች በአቀዱት መሰረት መስራታቸውን፣ የተጣለባቸውን ሃላፊነት መወጣታቸውን ለማረጋገጥ ግብ አስቀምጦ በጋራ መስራት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው አስታውቀዋል ።
ለዘርፉ ስኬታማነት የቋሚ ኮሚቴውና ቢሮው በቅንጅት እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።
ምንጭ፦ የክልሉ መ/ኮ
