የፍትሕ ሚኒስቴር የአስተዳደር ፍትሕ ላይ የሚደረጉ ትብብሮችን አስመለክቶ ከጂ አይ ዜድ (GIZ) ተወካዮች ጋር ዉይይት አካሄደ
******************
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የህግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ እና የተቋም ግንባታ የሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) ከጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ) ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር የአስተዳደር ፍትሕ ላይ የሚደረጉ ትብብሮች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዉ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ጀርመን የፌዴራል መንግስት አወቃቀርን የሚከተሉ አገራት እንደመሆናቸዉ መጠን የሚከተሏቸዉ ስርዓቶችም በዛዉ ልክ ተመሳሳይነት ያላቸዉ መሆናቸዉ የተገለፀ ሲሆን ከዚህ አንጻር የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ ማርቀቅ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ከጀርመን ልምድ የተወሰደ መሆኑን፣ ይህም በተለይ ክልሎች ይህን ህግ በሚያወጡበት ወቅት ትልቅ እገዛ እንዳደረገ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ ከማውጣት ባለፈ ህጉ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የተሻለ አተገባበር እንዲኖር ለማድረግ በቀጣይ ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ተግባራትና ለዚህም ከጀርመን ጋር ሊደረግ ስለታሰበው የልምድ ልዉዉጥ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጰያ መንግስት በፍትህ ሴክተሩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በሚያከናዉናቸዉ ሌሎች ተግባራት ዙሪያም ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይም በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ፣ የወንጀልና ፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ስርዓት እና ሌሎች ተግባራትን አስመልክቶ በቀጣይ መሰል ዉይይቶችን በማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
