በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ16 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተጠቆመ
(ሆሳዕና፣ነሐሴ 7/2017)በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ፋይናንሻል እና ፊዚካል ስራዎች አፈጻጸም ፣የክረምት ስራዎች ገቢ አሰባሰብ ለመገምገም እና በ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር የሚያስችል የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ እየተካሔደ ነው
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደግፌ መለሰ እንደገለጹት ክልሉ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ በተገቢው መንገድ ለመሰብሰብ ዘርፈ ብዙ ስራ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
20 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት አቶ ደግፌ በበጀት ዓመቱ ከ16 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ስለመሰብሰቡ አስረድተዋል።
እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ በክልሉ ከሌሎች አመታት በተለየ መልኩ ከፍ ያለ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደበት ዓመት እንደነበር አስታውሰዋል።
የክልሉ ገቢ እንዲሰበሰብ ከክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር የላቀ ሚና እንደነበረው አቶ ደግፌ በአብነት ጠቅሰዋል።
በማዘጋጃ ቤት 91 በመቶ እንዲሁም በመደበኛ ደግሞ 50 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ስለመቻሉም አቶ ደግፌ አስረድተዋል።
በተያዘው በጀት አመት የክልሉን ጸጋዎች መሰረት ያደረገ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት የተገኙ መልካም ልምዶችን በማስቀጠል እና ውስንነቶችን ፈጥኖ በማረም ለገቢው ሴክተር እድገት በትኩረት እንደሚሰራም ምክትል ኃላፊው አብራርተዋል።
ማህበረሰቡ በፈቃደኝነት ግብር የመክፈል ባህሉን እንዲያዳብር በማድረግ ረገድ በልዩ ትኩረት መሰራቱን አብራርተዋል።
ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ስኬታማ ህግ የማስከበር ስራ ማሳካት ተችሏል ያሉት ምክትል ኃላፊው የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ ደግፌ በንግግራቸው አመላክተዋል።
የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጠንካራ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል።
በክልሉ የታቀዱ የልማት ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ለማድረግ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
በመድረኩ ከክልል፣ከዞኖች፣ከልዩ ወረዳና ከከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ምንጭ፦ የክልሉ መ/ኮ
