የከተማ ምግብ ዋስትናና ስራ ፕሮጀክት የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ማጠቃለያ እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ማናበብ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት በቡታጅራ ከተማ ተጀምሯል።
(ነሐሴ 8/2017 ) በፌዴራል መንግስትና በዓለም ባንክ ድጋፍ በተመረጡ ከተሞች ለመተግበር በተመደበው በጀት በክልሉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን በማከናወንና ተጠቃሚዎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር በ2017 በጀት ዓመት የተጀመረውና የተከናወኑ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራዎች ላይ የክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴ አባላት እየገመገመ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል የመድረኩ ዓላማ በከተማ ምግብ ዋስትናና ስራ ፕሮጀክት የተከናወኑ የ2017 በጀት ዓመት ስራዎች አፈጻጸም መገምገምና የ2018 በጀት ዓመት ዋና ዋና ዕቅዶች ላይ መናበብና የጋራ ማድረግ ነው ብለዋል።
የመንግስት ራዕይ በሁሉም መስክ ከተሞችን ምርታማና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ በመሆኑ መንግስት ለከተሞች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝና ከተሞች በአንድ ታሪካዊ እጥፋት የሚገኙበትና አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡበት እንደሆነም አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል።
በከተሞች የሚከናወኑት ተግባራት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በመሆናቸው ለዜጎች ኑሮ መሻሻልና ምቹነት ትኩረት የሰጡ ናቸው ሲሉም አክለው ተናግረዋል።
የከተማ ልማት ሴፍትኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን በሁለት ዓይነት መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ያሉት አቶ ስንታየሁ በአካባቢ የልማት ስራዎች በማሳተፍና በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም እንደሆነም ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል ።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎች ወደ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ እንዲሸጋገሩ የሚያደርግ 57 ሺህ 454 ዜጎች በ5 ከተሞች ተጠቃሚ መሆናቸውንና 46 ሺህ 995 ዜጎች በአካባቢ ልማና 10 ሺህ 459 ዜጎች በቀጥታ ድጋፍ የሚሳተፉ ናቸው ብለዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የማስፈጸም አቅም ግንባታና መሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጨምር ኃይሌ ለስትሪንግ ኮሚቴው የ2017 በጀት ዓመት የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርት አቅርበዋል።
በአፈጻጸም የታዩ ድክመቶችና ጥንካሬዎችን ለይቶ የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥና እንደ ሀገር በ2018 በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዙ ስራዎችን ለማከናወን የተዘጋጀውን ዕቅድ የጋራ ለማድረግ ያግዛል ተብሏል ፡፡
የስትሪንግ ኮሚቴው በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሚመራና የፋይናንስ ቢሮ ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮና የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ አባል መሆናቸውን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
