በመስቃንና ማረቆ በአካባቢው የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለፀ።
ነሀሴ 08/2017ዓ.ም ቢሮው በመስቃንና ማረቆ አካባቢ እስካሁን ያለው የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ የክልል ፣የዞንና ልዩ ወረዳው የፀጥታ መዋቅሮችና ኮማንድ ፖስት ጋር በቡታጅራ ከተማ ገምግሟል።
ባለፉት ጊዜያት የተሰሩ ሰላምን የማፅናት ተግባራት ቀጣይም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ተጠናክሮ መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምናፀጥታ ቢሮና የክልሉ ፍትህ ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በገመገመበት ወቅት ገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮያጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ እንደገለፁት በአካባቢው የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል።
ቀጠናው ሁከትና ብጥብጥ በማድረግ ትርፍ አምራች የሆነውን ማህበረሰብ ተመፅዋች ለማድረግ የጥፋት ዓላማ ያደረጉ እንቅስቃሴዎች በተሰሩ ጠንካራ ስራ መቀልበስ መቻሉ አንስተዋል።
በተሰሩት ስራዎች ወንጀሎችና አጥፊዎች እርምጃ እንዲወሰድባቸው እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል ።
የህዝብ አንድነትና መከባበር ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ባህልና እሴቶቻችን በመጠቀም ሰላም የማፅናትን ተግባራት ማጠናከር እንደሚገባ አመላክቷል።
የሰላም ዕጦትና ፀር የሆኑትን ግጭት ጥላቻንና መናናቅን የሚያስከትሉት አሉታዊ ተፅኖ በመገንዘብ በፍቅርና በአብሮነት አሸናፊ በመሆን የአካባቢው ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ሰላምን በማረጋገጥ ተረጂነትና ኃላቀርነትን የሚፀየፍ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባም አንስተዋል።
ኮማንድ ፖስቱ በተለያዩ ጊዜያት በተሰሩ ስራዎች ልምድ በማካበቱን ጠቅሰው በአካባቢው ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ አርአያ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች መኖራቸው እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ቡድንተኝነት፤ጎሰኝነትና ራስ ወዳድነት የሰላም ጠንቅ ናቸው ያሉት ኃላፊው አብሮነትና አንድነት በሚያሰርፅ መልኩ በተለያዩ መድረኮች ሰፋፊ የግንዛቤ ስራዎች መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክመል አህመድ በአካባቢው የተፈጠረው ችግር በህግ አግባብ በመፍታት ዘላቃ ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ማህበረሰብ ያገኘው አንፃራዊ ሰላም በተገቢዉ መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ኃላው ግጭት ፈጣሪዎችንና በማህበራዊ ሚዲያ ግጭት የሚፈጥሩ አካላት መከታተል እንደሚገባ አንስተዋል።
በመድረኩ በኮማንድ ፖስት በቀረበው ሪፖርት የእስካሁኑ አፈፃፀሙ የተመዘገቡ ውጤቶችና በሂደቱ የታዩ ጉድለቶችን በመለየት በዝርዝር ተገምግመዋል።
በአካባቢው የተከሰተው የፀጥታ ችግር ወደመደበኛ ሰላም ለማምጣት መላው ህብረተሰብ ወጣቶች የአካባቢ አስተዳዳር አካላት ከፀጥታ ሀይል ጎን ሆነው ለተሰሩ ስራዎች ቢርው ምስጋና ሰጥቷል።
በሂደቱ ፈተናዎችን በማሻገር በእውቀት በጥበቡ ቁርጠኝነት በመመራቱ ከነበሩበት ውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታ መሻገር የተቻለ መሆኑን ተነስቷል።
በአጠቃላይ በተሰጡ ግቦች መሰረት እስካሁን ያልተከናወኑ ተግባራት ተለይተው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
