Skip to main content

የሉሲ(ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላት በመካከለኛው አውሮፓ በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት በአዲስ መልክ ያስተዋውቃሉ - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ

ነሐሴ 9/2017)፦ የሉሲ(ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላት በመካከለኛው አውሮፓ በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት በአዲስ መልክ እንደሚያስተዋውቁ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ለሚሄደው የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላት አሸኛኘት አድርጓል።

በመርሀ ግብሩ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ ተገኝተዋል።

ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በዓለም ከምትታወቅበት መለያ አንዱ የሰው ዘር መገኛነቷ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ገጽታ ለመገንባት እንዲሁም ለዓለም ለማስተዋወቅ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላት ወደ ቼክ ሪፐብሊክ እንደሚሄዱ አስታውቀዋል።

ቅሪተ አካላቱ በፕራግ ብሔራዊ ሙዝየም ለህዝብ እይታ እንደሚቀርቡም ነው የገለጹት።

ቅሪተ አካላቱ በቼክ ሪፐብሊክ በሚኖራቸው ቆይታ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ገልጠው እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት በአዲስ መልክ እንደሚያስተዋውቁ ሚኒስትሯ አመላክተዋል።

በተጓዳኝም የሁለትዮሽ የንግድ ፎረሞች እና ሌሎች ሁነቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

የፕራግ ብሔራዊ ሙዝየም ዳይሬክተር ጀነራል ሚካኤል ሉኬሽ በበኩላቸው የቅሪተ አካላቱ በሙዝየሙ ለእይታ መቅረባቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ቅሪተ አካላቱ በታሪካዊ ቦታ ላይ ለእይታ እንደሚቀርቡ ጠቁመው ይህንን እውን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላት ለሰው ዘር አመጣጥ ምርምር ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ቅርሶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
#ኢዜአ

Image
የሉሲ(ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላት በመካከለኛው አውሮፓ በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት በአዲስ መልክ ያስተዋውቃሉ - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ