በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የተሰራው ቅንጅታዊ ስራ ትምህርት ሊወሰድበት የሚችል እንደሆነ ተገለጸ።
ጳጉሜ 3/2017 ዓ.ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 ዓ/ም ዕቅድ የሚመክር ጉባኤ በቡታጅራ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
ጉባኤው “የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ ክብር ያረጋገጠ የፍትህ ስርዓት እንገነባለን!” በሚል መሪ ቃል ነው ከሴክተሩ አመራር፣ ከባለድርሻ አካላት እና ከህዝብ ክንፍ አባላት እየተካሄደ የሚገኘው።
አቶ አክመል አህመዲን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል በመደረጉ በሴክተሩ በተሰሩ ስራዎች ላይ ከፍ ያለ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ባለፈው በጀት አመት የክልሉ ሰላም የተረጋጋ እንዲሆን ግጭት አባባሽ ማህበራዊ ሚዲያዎች አደብ እንዲገዙ ፣ በርካታ የተወረሩ የከተማናና ገጠር መሬቶችእንዲመለሱና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የተሰራው ቅንጅታዊ ስራ ትምህርት ሊወሰድበት የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።
በቢሮ ኃላፊው አቶ አክመል አማካይነት የሴክተሩ የ2017 በጀት አመት አፈጻጸም ሪፖርት ለመድረኩ እየቀረበ ይገኛል።
በ2017 በጀት አመት አፈጻጸም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የዞንና የልዩ ወረዳ መዋቅሮች የማበረታቻ ዋንጫና ሰርተፊኬት የ2018 በጀት አመት ዕቅድ የግብ ስምምነት እንደሚፈረም ለማወቅ ተችሏል።
በመድረኩ የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ እና የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሴክተሩ ተዋንያን እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን
