Tue, 10/22/2024 - 18:41
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የሀላባ ክላስተር በሀገር አቀፍ ጳጉሜ 2/2016 ዓ/ም የሚከበረውን የሪፎርም ቀን በድምቀት አከበረ።
### ###########################
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ክላስተር ጳጉሜ 2 “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የሪፎርም ቀን በሀላባ ከተማ ሴራ አዳራሽ ከክላስተሩ መስሪያ ቤቶች አመራሮችና ፈፃሚዎች ጋር አክብረዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክመል አህመዲን ሲሆኑ ባስተላለፉትም መልዕክት
የሪፎርም አስፈላጊነትን ስንገነዘብ የሚገጥመንን መሰናክል በጋራ በማለፍ ፍትህ ፣እኩልነት ና ሰላምን በመገንባት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በፍትህ ፣በትምህርት ፣በፈጠራ እና በማህበረሰብ አገልግሎት ሁላችንም አዎንታዊ ለውጦችን ለማምጣት መሥራት እንደሚገበ በማስገንዘብ፤ ለክልሉ ህብረተሰብ መሠረታዊ የፍትህ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በፍትህ ዘርፉ መልካም አስተዳደርን በማስፈን በህገ-መንግስቱ የተረጋገጠው የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማጠናከርና በማስከበር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል የፍትህ አገልግሎት ተደራሽነት የማስፋት እና ክልላዊ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ በንግግራቸው ከማህበረሰባችን የተጣለብን ኃላፊነት እና አደራን በፍፁም ቆራጥነት መወጣት እንዳለብን በመግለፅ እና በፍትህ ዘርፍ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መከላከል እንዳለብን ገልፀው ህብረተሰቡም በፍትህ አገልግሎት ላይ ያለውን አመኔታ ለማረጋገጥ የዘርፉ አመራሮች እና ፈፃሚዎች በቁርጠኝነት ለለውጥ ሊነሱ እንደሚገባ አሳስበዋል ።
እንደክላስተር የተዘጋጀው የሪፎርም ሰነድ በአቶ ጌታሁን ፍቅሩ እና በአቶ መኮንን ተሻለ ቀርቦ በተሳታፈዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
በመጨረሻም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በአቶ ኤርሲኖ አቡሬ እና በፍትህ ቢሮ ኃላፊ በአቶ አክመል አህመዲን በተነሱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ምላሽ እና ሀሳብ በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።
ጳጉሜ 2 /2016 ዓ/ም
ዘገባዉ፤ የፍትህ ቢሮ መንግስት ኮሙኒኬሽን
Image
