Skip to main content
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፍትህ ቢሮ በክልሉ ለሚሰሩ ጠብቆች ሙያዊ ግዴታዎችና የባለድርሻ ሚናን አስመልክቶ ውይይት ለማድረግ እና የክልሉን የጠበቆች ማህበር ለማቋቋም የውይይት መድረክ አካሄደ።###################
############################
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ታህሣስ 15/ 2017 ዓ/ም በሀላባ ቁሊቶ ሴራ አዳራሽ ባካሄደው መድረክ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሶኖ አቦሬን ጨምሮ የተወካዮች ምክር ቤት የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ ሮ መሠረት ወ/ሰንበት ፤ የርዕሰ መ/ሩ የመልካም አስተዳደር እና የህግ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ኑርዬ ሱሌ ፤ የርዕሰ መ/ሩ ዋና አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስ እና ባለ ድርሻ አካላት ፡፤በክልሉ የሚገኙ ጠበቆች የተገኙ ሲሆን በዕለቱም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክመል አህመዲን ሲሆኑ በንግግራቸውም ጠበቆች በህግ የተጣለባቸውን ሙያዊ ግዴታ አክብረው ከመሥራት አንፃር የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ጠቅሰዋል ።
በመቀጠልም በንግግራቸው ጠበቆች የፍትህ አስተዳደሩ አካል በመሆናቸው ዋነኛ አላማቸውም ፍትህ እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በመሆኑ የግራ ቀኙ የክርክር ሂደት ፍትሃዊ ሆኖ እንዲቀጥል ሚናቸው እጅግ ከፍተኛ ነው ብለዋል ።
በማከልም የክልሉ ፍትህ ቢሮ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት በክልሉ ለሚሠሩ ጠበቆች ፈቃድ ከመስጠትና ከማደስ ባሻገር ፈቃድ የተሰጣቸው ጠበቆች ሙያዊ ግዴታቸውን አክብረው እንዲሰሩ ድጋፍ ክትትል እና ቁጥጥር ያደርጋል ፤ ጠበቆች ለፍትህ አስተዳደሩ መጠናከር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ።
ጠበቆች ሙያዊ ነፃነታቸው ተጠብቆ በየጊዜው አቅማቸው እየጎለበተ እንዲሄድ እና የጥብቅና አገልግሎት ተጠቃሚው ዜጋ ድርጅታዊ ዋስትና እንዲኖረው ለማስቻል ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማስፈን የጠበቆች ማህበር ማቋቋሙና ጥብቅናው የሚመራበት ሥርዓት መዘርጋቱ የክልሉን የጥብቅና ሙያ ከሀገርም አልፎ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ ያደርገዋል ።በዚህም መሠረት በዛሬው ዕለት አንዱ የሚጠበቀው ተግባር የጠበቆች ማህበር መመስረት በመሆኑ ይህ ማህበር ጠንካራና የአባላቱን እና የደንበኞችን መብት የሚያስከብር እንዲሆን ግልጽና ፍትሃዊ ስብጥሩን የጠበቀ እና ፆታንም ያካተተ የሆነ ምርጫ እንደሚካሄድ እምነታቸውን ገልጸዋል ።
በመቀጠልም የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ኘረዝደንት አቶ ኤርስኖ አቡሬ የዕለቱ የክብር እንግዳ መልዕክት በማስተላለፍ መድረኩን በይፋ የከፈቱ ሲሆን በንግግራቸውም ጠበቆች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሥነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ።
የቢሮው የጠበቆችና ሲቪክ ማህበራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸብር አዲሱ ለውይይት የተዘጋጀውን ሰነድ አቅርበው ተሳታፊዎች ጥልቅ ውይይት አድርገውበታል።
በመጨረሻም በክልሉ የጥብቅና ፈቃድ አውጥተው በመሥራት ላይ ካሉ ከሁሉም ዞኖች ከመጡ ጠበቆች መካከል በሥነ-ምግባር የተመሰከረላቸው አርአያ የሚሆኑ ማህበሩን በብቃት መወከል የሚችሉ የማህበሩ ኘሬዝዳንት፤ምክትል ኘሬዝደንት እና ሰባት አስፈጻሚ አባላትንም ጭምር በመምረጥ ማህበሩን አቋቅሟል።
Image
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፍትህ ቢሮ በክልሉ ለሚሰሩ ጠብቆች ሙያዊ ግዴታዎችና የባለድርሻ ሚናን አስመልክቶ ውይይት ለማድረግ እና የክልሉን የጠበቆች ማህበር ለማቋቋም የውይይት መድረክ አካሄደ።