Skip to main content

ከሰንበት እስከ ሰንበት የገበያ ማዕከል ግንባታ 
የኑሮ ውድነት ጫናን በመቀነስ  የአምራቹንና ሸማቹን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ተግባር መሆኑን  የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ

(ሆሳዕና ፣ሰኔ 27/2017) ቢሮው  በዱራሜ ከተማ ለሚገነባው  ከሰንበት እስከ ሰንበት ዘመናዊ የግብይት ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማኖር መርሐ ግብር አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠዉ እንደገለፁት  
የሰንበት ገበያ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በህገወጥ ነጋዴዎች ሳይበዘበዙ  ኑሮ ውድነትን ለማቃለል ሳምንቱን በሙሉ የንግድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ ብሎም አርሶ አደሩን ከሸማቹ ጋር  በቀጥታ በማገናኘት  የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ተግባር እንደሆነም ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱም 15 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት የሚገነባ እንደሆነ ገልፀው በውስጡ ከ34 በላይ ዘመናዊ ሱቆች እና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ላይ የያዘ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ በ4 ወራት ተጠናቆ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ሁሉም የድርሻውን እንደወጣ ሃላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ  እንደተናገሩት የአርሶአደሩን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አምራቹን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘት ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይትን በመፈጸም የኑሮ ውድነትን የሚቀንስ ፕሮጀክት እንደሆነ ገልፀዋል።

ህብረተሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር የሚያደርግና በዘላቂነትና በቋሚነት  የንግድ ስርኣቱን  የሚያሳልጥና ዘመናዊ የግብይት ስርዓት እንዲኖር የሚያደርግ ነው  ሲሉም ገልፀዋል።

የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታረቀኝ ተስፋዬ በበኩላቸው ህብረተሰቡ የተሻሻለ ኑሮ እንዲኖርና ሸማቾችና አቅራቢዎች ስርዓት ባለው መንገድ የንግድ ስርዓትን እንዲያቀላጥፍ የሚረዳና ጤናማ ግብይት እንዲኖር የሚረዳ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ  የክልል፣የዞን እና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በአድነው አሰፋ

Image
ከሰንበት እስከ ሰንበት የገበያ ማዕከል ግንባታ