Skip to main content

በክልሉ ከ500 ሚሊየን በላይ ችግኞች ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል - አቶ ኡስማን ሱሩር

(ሆሳዕና፣ሰኔ 30/2017)በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነገ ሀምሌ 1/2017 ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ እና የገጠር ኮሪደር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር እንደሚካሔድም ተመላክቷል

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ነገ ሀምሌ1/2017 ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ እና የገጠር ኮሪደር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ይካሄዳል ብለዋል።

በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ በሚካሄደው ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ከ500 ሚሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉም ኃላፊው በመግለጫቸው አመላክተዋል።

በክልሉ ከ310 ሚሊየን በላይ የፎራፍሬ፣የቡና የእንስሳት መኖ እና ሌሎች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ እንደሚካሔድ ኃላፊው አብራርተዋል።

እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ ከ190 ሚሊየን በላይ አላማ ተኮር የደን ልማትን ማዕከል ያደረጉና ለአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ።

በክልሉ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ከ1ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ልዩ ልዩ ችግኞችን መትከል ተችሏል ያሉት ኃላፊው በዚህም ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ ፣ስነ ምህዳራዊና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ማግኘት ስለመቻሉም አቶ ኡስማን በአብነት ጠቅሰዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋምና ለመቀነስ የተራቆቱ ተራራዎችን በደን የመሸፈን፣የተመናመኑ ደኖችን መልሶ ማልማት፣ግድቦችን፣ሀይቆችን እና ወንዞችን  ከደለል የመከላከል ስራ ትኩረት እንደተሰጠውም ኃላፊው በመግለጫቸው አመላክተዋል።

ባለፉት ስድስት አመታት በተካሔደ የአካባቢ ጥበቃ ስራ  ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ሀገራችን ለአለም ማህበረሰብ ተምሳሌታዊ ተግባር ማከናወኗን ነው አቶ ኡስማን የጠቆሙት።

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል እና ለኢኮኖሚያችን ማንሰራራት መንስኤ የሆኑ የችግኝ ተከላ ማካሔድ መቻሉን ኃላፊው አብራርተዋል።

በክልሉ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተከትሎ በዘርፉ የላቀ ውጤት ስለመመዝገቡም አቶ ኡስማን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አከባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ
አቶ አብርሀም መጫ በበኩላቸው በክልሉ በነገው እለት በሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዱ እና አላማ ተኮር ችግኞች ይተከላሉ።

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ  የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እስከሚጠናቀቅ ባለው ሂደት ከ1ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉም አቶ አብርሐም በመግለጫቸው አብራርተዋል።

ለሰው ልጆች እና ለሌሎች ፍጡራን የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት መሆኑን ተከትሎ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ልዩ ትኩረት እንደሚያሻም ጠቁመዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጎርፍ፣ድርቅ፣ሰደድ እሳት፣የመሬት መራቆት፣የዝናብ መጠን ማነስ እና የዝናብ ስርጭት መዛባት እየተከሰተ ስለመሆኑም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

የለውጡ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በሰጠው ልዩ ትኩረት ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑም አቶ አብረሀም ተናግረዋል።

ላለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር መካሔዱን ተከትሎ የደን ሽፋን ማደግ፣የዝናብ መጠን መጨመር፣የዝናብ ስርጭት መስተካከል፣የሙቀት መጠን መሻሻል እና መሰል ውጤቶች ስለመስተዋላቸውም ኃላፊው በአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር የውሃ አካላት መጨመሩን ተከትሎ ውሃን ማዕከል ያደረገ የግብርና ስራ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረም  አቶ አብርሀም በመግለጫቸው አስረድተዋል።

በነገው እለት ከሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በተጓዳኝ የገጠር ኮሪደር ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር እንደሚካሔድም ተመላክቷል።

በተስፋዬ መኮንን 

Image
በክልሉ ከ500 ሚሊየን በላይ ችግኞች ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል