Skip to main content

ባሳለፍነው አመት የክልሉን ጸጥታ በማስከበር የህዝቡ ሰላም እንዲጠበቅና የክልሉ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ የተሰሩ ፖሊሳዊ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

በቀጣዩ አመት በክልሉ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የብሄር ብሄረሰቦች በኣልና ሀገራዊ ምርጫ ከወዲሁ የተሟላ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፖሊስ ኮሚሽኑ አስታውቋል ።  

በተጠናቀቀው በጀት አመት የክልሉን ጸጥታ በማስከበር የህዝቡ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቅና የክልሉ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ የተሰሩ ቅንጅታዊ የፖሊስ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

ኮሚሽኑ የ2017 በጀት አመት አፈጻጸሙን የዞንና ልዩ ወረዳ የፖሊስ አመራሮች በተገኙበት በሆሳዕና የገመገመ ሲሆን በዚሁ ወቅት እንዳለው ግጭቶችን አስቀድሞ በመከላከል የክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሺመልስ ካሳ እንደገለጹት እነዚህ ፖሊሳዊ ተግባራት የክልሉ ህዝብ ሰላሙ ተጠብቆ ያለ ችግር ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

በክልሉ ብቻ ሳይሆን ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመቀናጀት በአዋሳኝ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን የተደረገው ጥረት አበረታች መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል ።

መዋቅሩ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመቀናጀት የጸጥታ ችግሮችንና አዝማሚያዎችን  መነሻ ባደረገ መልኩ የሰራቸው ተግባራት አንጻራዊ ሰላም እንዲሰምፍን ማስቻላቸውን ያነሱት ኮሚሽነሩ በተለይም የክልሉ የግጭት ተጋላጭ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከተሞች የሰፈነው አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ የውጤታማ ፖሊሳዊ ስራዎች አንዱ ማሳያ እንደሆነም ኮሚሽነር ሺመልስ አብራርተዋል ።

በክልሉ በተለይ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ስራዎች፣ የገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤት ሚና፣ የመረጃ ልውውጥ ስርኣትና የሰው ሃይል ማጠናከር ስራዎች ስኬታማ እንደነበሩ ገልጸዋል ።

ያም ሆኖ የትራፊክ ፖሊሶች ስነ ምግባርና የመኪና አደጋ መበራከት ችግሮች ልዩ ትኩረት እንደሚሹ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብርሃም ቲርካሶ በበኩላቸው ወንጀል መከላከል በፖሊስ ብቻ ውጤታማ ስለማይሆን የህዝብ ተሳትፎን ማጠናከርና  ሳይንሳዊ የፖሊስ ስራን ማጎልበት ይገባል ብለዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው የወንጀል መከላከል ማዕከላትን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል ።

የተሽከርካሪ አደጋና የትራፊክ ፖሊሶች ስነ ምግባር ከፍተኛ ችግሮች እየሆኑ መምጣታቸውን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነር አብርሃም ችግሮቹን ለመቅረፍ ቅንጅታዊ አሰራር መጎልበት እንዳለበት ተናግረዋል ።

በግምገማ መድረኩ የቀረበ ሪፖርት እንደሚያሳየው ባሳለፍነው በጀት አመት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ በርካታ የተሽከርካሪ አደጋዎች ምክንያት 180 የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ችግሩ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ሁለንተናዊ ቀውስ እየፈጠረ በመሆኑ ሁሉም አካላት ተቀናጅተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በአጽንኦት ተነስቷል።

ፖሊስ ኮሚሽኑ ከ2017 አፈጻጸም መነሻ በቀጣዩ አመትም የተሻሉ ፖሊሳዊ ስራዎችን በቅንጅት በመፈጸም በክልሉ አዘጋጅነት የሚካሄደውን 20ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በኣልና ሀገራዊ ምርጫ ያለ ችግር ችግር እንዲካሄዱ ከወዲሁ የተሟላ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል ።

ምንጭ : የክልሉ መ/ኮ

Image
የክልሉን ጸጥታ በማስከበር የህዝቡ ሰላም እንዲጠበቅና የክልሉ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ የተሰሩ ፖሊሳዊ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።