የክልሉ ፍትህ ሴክተር ተቋማት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ያስገነቧቸውን ቤቶች ለባለቤቶቹ አስረከቡ
**
ነሃሴ 30/2018)፣የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ሴክተር ተቋማት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ያስገነቧቸውን ሁለት የመኖሪያ ቤቶች ለባለቤቶች አስተላልፈዋል።
ተቋሟቱ የአቅመ ደካሞቹን የቤት ግንባታ ሀምሌ 14/2018 ማስጀመራቸው ይታወቃል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ኤርስኖ አቡሬ ተቋሙ የማህበራዊ ሀላፊነት ለመወጣት በርካታ ስራዎችን እየፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።
ደካሞችን ለመደገፍ የተጀመረውን ስራ በማጠናከር የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ባህል ማድረግ ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዛሬው ዕለትም የፍትህ አካላትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት በ1.2 ሚሊዮን ብር በጋራ የተገነባ የመኖሪያ ቤት አስረክቧል
የርዕሰ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ ንጉሴ አስረስ ዶ/ር በክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በልዩ ትኩረት እየተመራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።
በክልሉ በሁሉም ዘርፍ በተሰራው ስራ እምርታ መጥቷል ያሉት ዋና አማካሪው የበጎ ተግባሩ ለዜጎች እፎይታን የሠጠና የመንግስትና የማህበረሰቡን ትስስርን እያጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በጉልበቱ ፣በእውቀቱና በገንዘቡ ጠንካራ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረው እስካሁንም በክልሉ ከ13 ቢሊዮን በላይ ብር ተሳትፎ ማድረጉን ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ አክመል አህመድን በበኩላቸው የመረዳዳትና የመተጋገዝ አካል አንዱ የሆነውን ለአቅመ ደካማ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ገንብቶ አስረክቧል ብለዋል።
ግንባታውን የፍትህ ቢሮ እና የማረሚያ ተቋማት በጋራ ያስገነቡት መሆኑን ገልፀው ለቤቱ የሚያስፈልጉ ሙሉ የቤት እቃዎች የተሟላለትና ለእናታችን ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆን የ50 ሺ ብር ተጨማሪ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ተግባሩ ዜጎች የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖራቸው ያደርጋል ያሉት አቶ አክመል በአጠቃላይ ለቤቱ ግንባታና የቤት ቁሳቁስ 1 ሚሊዮን 200ሺ ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
የሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ገመዳ መሀመድ በበኩላቸው መንግስት በዜጋ ተኮር ስራዎች የተለያዩ ማህበራዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ተጠቃሚ ማድረጉንና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
አባታቸውን በሞት ያጡ 4 ልጆችና 2 ወላጅ አልባ በድምሩ የ6 ልጆች አሳዳጊ የሆኑት ወ/ሮ መድሀኒት ሀይሉ መንግስት ያደረገላቸው የተሟላ ድጋፉ ለልጆቻቸውና ለራሳቸው ተስፋን እንደጨመረላቸው ተናግረዋል።
ሁለተኛው የቤት ድጋፍ የተደረገላቸው እናት ልጃቸው የሀገር መከላከያን እያገለገለ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ አይነቴ ቦጪሶ ደግሞ ድጋፉ ከሰው ጋር እኩል መኖር እንዲችሉ ያስቻላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በቁልፍ ርክክቡ ወቅት የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን ለቤቶቹ ግንባታ ስኬት ድጋፍ ያደረጉ አካላትን በሙሉ አመስግነዋል።