Skip to main content

ሙስናን በቅንጅት በመከላከል የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት የህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች  ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ

(ሆሳዕና፦ ሀምሌ 8/2017) ቋሚ ኮሚቴው  የክልሉን ስነ-ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምን ገምግሟል።

የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ   ወ/ሮ መሰረት ወ/ሰንበት እንዳሉት ሙስናን በቅንጅት በመከላከል  የህግ የበላይነት  እንዲሰፍን አበክሮ ሊሰራ ይገባል።

በፀረ ሙስነ ትግል ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የተካሄደበት አግባብ ጥሩ ሆኖ ሙስናን በመከላከልና ሙስናን የሚጸየፍ ዜጋን ለማፍራት ሌተ ቀን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በቅድመ መከላከል ከመመዝበር የዳነና  የተመለሰ የመንግስት ሀብትን በጥሬ ገንዘብና በአይነት ለማስመለስ በርካታ ስራዎች የተሰራ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መረባረብ ያስፈልጋል ሲሉ ወ/ሮ መሰረት ተናግረዋል።

የስነ ምግባር አውታሮችን በማደራጀት  የባለሙያዎችን መረጃ በሚገባ ለመሰብሰብ የተሞከረበት አግባብ ጥሩ ነው ብለው የስነ ምግባር አውታሮችን ድጋፍና ክትትል እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መደረጉ  አበረታች እንደሆነ ገልፀዋል።

ሀብትን ማሳወቅና  ምዝገባ መረጃ ማስተዳደር የተጀመረውን አሰራር በቀጣይ በልዩ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ብለው የውስጥና የውጪ አሰራር ስርዓትን በማጠናከር ተቋሙ ለህዝብ ተጠቃሚነት ከምን ጊዜ በላይ መስራት ይጠበቃል ሲሉም ገልፀዋል።

ህግን በሚጥሱና ብልሹ አሰራርን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ አወሳሰድ ላይ ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ በቀጣይ ከሚመለከታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የክልሉ ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ደንና አከባቢ ጥበቃ ቢሮን፣የፕላን መሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ዋና ኦዲት መስሪያ ቤትን እና የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ባህል ቱሪዝም ቢሮን የ2017 አፈጻጸምን የገመገሙ ሲሆኑ ከቋሚ ኮሚቴቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ከተቋማቱ ቢሮ ኃላፊዎችና ማኔጅመንት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
ምንጭ :- የክልሉ መ/ኮ

Image
ሙስናን በቅንጅት በመከላከል የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት የህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች  ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ