የገዢ ትርክትን ቀጣይነት ባለው መልኩ በማስረጽና አንድነትን በማጠናከር የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን መሻገር እንደሚገባ ተገለጸ።
ሀላባ: ጳጉሜ/1/2017
ጳጉሜ-1 የጽናት ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀላባ በቁሊቶ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
ቀኑን በክላስተሩ የሚገኙ የክልል፣ የዞን፣ የቁሊቶ ከተማ አስተዳደርና የዌራ ወረዳ የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች እና ሰራተኞች እንዲሁም የከተማው ማህበረሰብ በጋራ አክብረውታል።
ቀኑን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክመል አህመዲን የጷጎሜ ቀናትን አከባበር አላማ አስረድተው፤ የዘንድሮውን የጷጎሜ ቀናት አከባበርን ልዩ የሚያደርገው ታላቁን የህዳሴ ግድብ አጠናቀን በምንመርቅበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል።
በዕለቱ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ትርኢት የቀረበ ሲሆን "ጽኑ መሠረት ብርቱ ሀገር" በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በቀረበው ሰነድ ኢትዮጵያ የአድዋ ድልን ጨምሮ ሀገር በማጽናት ረገድ የተጎናጸፈቻቸውን በርካታ የጦር ሜዳ እና ዲፕሎማሲያዊ ድሎች እንዲሁም ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በስፋት ተዳስሷል።
የቀደመው ትውልድ ያጸናትን ሀገር አሁን ያለው ትውልድ ሀገሩን በመጠበቅ እና የልማት ስራዎችን በጽናት በማከናወን ተምሳሌት መሆን እንደሚገባው በፓናል ውይይቱ ተመላክቷል።
የገዢ ትርክትን ቀጣይነት ባለው መልኩ በማስረጽና አንድነትን በማጠናከር የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን መሻገር ይገባል ተብሏል።
አቶ ኤርሴኖ ሀቡሬ - የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ከፍተኛ የክልልና የዞን የስራ ኃላፊዎች በዚሁ መድረክ ተገኝተዋል።
የቀኑ አከባበር የብሄራዊ መዝሙር ተዘምሮ ተጠናቋል።
መ/ኮ
