የትጋት ምሳሌ ከመሆን እስከ እርቅ አባትነት ስማቸው የሚነሳው የሰላም አባት ሀጂ ከድር
ሀጂ ከድር ተካ አርሶ አደርና የሀገር ሽማግሌ ናቸው። በባህላዊ ዳኝነት ሥራቸው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለረጅም ጊዜ ሲያገለግሉ የቆዩት ሀጂ ከድር ተካ ዛሬም አንቱታን ያተረፉባቸውን አያሌ ሥራዎች እየሰሩ ይገኛሉ።
ሀጂ በ80ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው። ውልደታቸውና ዕድገታቸው በስልጤ ዞን፣ ሳንኩራ ወረዳ፣ ዓለም ገበያ ውስጥ ነው።
ሀጂ ከድር ተካ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የተራራቁትን በማቀራረብ በብዙዎች ዘንድ የተመሰከረላቸው አርሶ አደርና የሀገር ሽማግሌም ናቸው።
ገና በወጣትነት የዕድሜ ክልል እያሉ የቀበሌ አስተዳደርና ሚሊሻ ሆነው የሳንኩራን ህዝብ በቅንነት ማገልገላቸውን ብዙዎች ይመሰክራሉ።
ሀጂ ከድር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመቀበልና በመተግበር ረገድ ግንባር ቀደም ከሚባሉ አርሶ አደሮች መካከል ናቸው።
በጓሯቸው ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያና መሰል አትክልትና ፍራፍሬን አልምተው ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ኑሯቸውን ለማሻሻል ጥረት ከሚያደርጉ ብርቱ አርሶ አደሮች መካከል ናቸው።
ሀጂ ከድር ተካ የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን ሕይወት የሚመሩት በግብርና ሥራ በሚያገኙት ገቢ ነው። ከመተዳደሪያ ሥራቸው ጎን ለጎን የተጣለባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ምንም ቅድመ ሁኔታ ሳያቀርቡ ሁሌም ይተጋሉ።
ሀጂ አወል ኑሪ በሳንኩራ ወረዳ የሀገር ሽማግሌ ናቸው። ከሀጂ ከድር ተካ የሕይወት ተሞክሮ ብዙ መማር ይቻላል ይላሉ። ሀጂ አወል በቤተሰባቸው ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት እርቀ ሰላም ለማውረድ ሀጂ ከድር ተካን ሽምግልና ይጠይቃሉ። ሀጂ ከድርም በተጠየቁት መሰረት በባህላዊ ዳኝነት አግባብ የሁለቱንም ወገን አቤቱታ ሰምተው ሚዛናዊ ፍርድ በመስጠት እርቅ እንዲወርድ አድርገዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ማንነት ሲፈተሽ ፕሮግራም ላይ ቀርበው የሕይወት ልምድና ተሞክሯቸውን ያካፈሉት ሀጂ ከድር ተካ በማህበረሰቡ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የተረጋጋ ማህበረዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲዳብር ሁሌም ይተጋሉ።
በመሀመድ ፊጣሞ
