በ2017 በጀት አመት 16 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።
(ሆሳዕና፣ ሰኔ 30/2017) ፣ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ከነገ ጀምሮ ባሉት 10 ተከታታይ ቀናት ግብራቸውን እንዲከፍሉ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
በ2017 በጀት አመት 16 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው እንዳለው በበጀት አመቱ 20 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ከተለያዩ የገቢ አርእስቶች ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከ አሁን ባለው ሂደት 16 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።
የቢሮው ሃላፊ ተወካይና የደንበኞች አገልግሎት የታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ደግፌ መለሰ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የክልሉ መንግስት ወጪን በሚሰበሰብ ገቢ ለመተካት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የገቢ አማራጮችን ለማስፋት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በተለይም እንደ ሀገር የተቀመጠውን የገቢ ዘርፍ ሪፎርም በተሟላ መልኩ ለመተግበር፣ የታክስ አሰባሰብን በማዘመንና ቀጣፋ አገልግሎት በማቅረብ የገቢ አቅምን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
ክልሉ ገቢን ቁጥር አንድ አጀንዳ በማድረግ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ተገቢውን ታክስ በመሰብሰብ የክልሉ ወጪዎች በውስጥ ገቢ ለመሸፈን ጥረት መደረጉን አቶ ደግፌ አስታውቀዋል ።
የዘርፉን ግቦች ለማሳካት ቢሮው 5 የትኩረት መስኮችን ነድፎ መንቀሳቀሱን የጠቆሙት አቶ ደግፌ በተለይም የዜጎችን ታክስን በፈቃድኝነት የመክፈል ባህል ለማሳደግ፣ ዲጅታል ስርኣትን ላመዘርጋትና የግብር ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራቱን አብራርተዋል ።
የኤሌክትሮኒክ የግብር መረጃ ፋይሊንግ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ስርጭት፣ የደረሰኝ ማጭበርበርን በመከላከል ረገድ የተገኘው ተሞክሮ አበረታች እንደነበር ተናግረዋል ።
የገቢ አማራጮችን ለማስፋትና የዘርፉን ህጎች ለማጠናከር የተደረጉ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ኪራይና የግብርና ገቢ ግብር አዋጅ፣ የማዘጋጃ ቤት የገቢ አይነትና ምጣኔ ተመን ደንብ፣ የታክስ አስተዳደር ደንብ የኢንቨስትመንት እና የማዕድን ደንብ መተግበራቸው ለአፈጻጸሙ አስተዋጽኦ ማበረከታቸውንም አብራርተዋል ።
በበጀት አመቱ 13ሺ የሚጠጉ አዳዲስ ግብር ከፋዮች መመዝገባቸውን ያነሱት አቶ ደግፌ 1ሺ የሚሆኑት ደግሞ የደረጃ ሽግግር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል ። እንደ አቶ ደግፌ ገለጻ በክልሉ 20 ሺ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በቴሌ ብር ግብራቸውን እንዲከፍሉ የሚያስችል ዝግጅትም ተጠናቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ በተገኙ 784 ግለሰቦች በተወሰደ አስተዳደራዊ ቅጣት 41 ሚሊዮን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን ኦዲት ከተደረገ የተሰወረ ታክስ ግኝት 236 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ዘጠና ስምንት ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል ።
ከውዝፍ እዳ 333 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ሲሉም አክለዋል።
እንደ አጠቃላይ በክልሉ ከመደበኛ ገቢ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን እና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን በድምሩ 16 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን አፈጻጸሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ5 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወይም የ49% ብልጫ እንዳለው አቶ ደግፌ አስረድተዋል ።
አቶ ደግፌ በመግለጫቸው እንዳብራሩት የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ከነገ ጀምሮ ባሉት 10 ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ በመሆኑ ሁሉም የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ ፦ የክልሉ መ/ኮ
