በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአንድ ጀንበር 6 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ
ሆሳዕና ፣ ሐምሌ 21፣ 2017 የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ በአንድ ጀንበር 6 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል በክልል ደረጃ ዝግጅት ተደርጓል አለ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክልሉ 502 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ።
በዓመቱ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 304 ሚሊየን የፍራፍሬ፣ የቡናና የጥምር ደን ሲሆኑ÷ ቀሪ 198 ሚሊየን ችግኞች ደግሞ ለደን ልማት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
በዚህም 161 ሺህ 925 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ዝግጅት ተደርጎ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በሚከናወነው በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ክልሉ 6 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።
በአንድ ጀንበር የተከላ ፕሮግራም 2 ሺህ 486 ሄክታር መሬት ለመሸፈን መታቀዱን አንስተው÷ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ሕብረተሰቡ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በየአካባቢው በነቂስ ወጥቶ በመሳተፍ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል።
(ኤፍ ኤም ሲ)
