Skip to main content

የቅጣት አወሳሰን መመሪያ 3/2017 እና የፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ዙሪያ የዐቃቢያነ ህግ አቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተካሄደ 

ሀላባ፣ ግንቦት 15/ 2018 ዓ.ም 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፍትህ ቢሮ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 እና በፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ዘርፍ የዐቃቢያነ ህግ ሚናን ለማጠናከር ያለመ ሥልጠና ለክልሉ፣ ለዞን እና ለልዩ ወረዳ ዐቃቢያነ ህጎች በሆሳዕና ከተማ ለሁለት  ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረዉ ስልጠና ተጠናቀቀ ። 

በሥልጠናው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የኮርፖሬት ዘርፍ  ኃላፊ  አቶ ሰላሙ ዳንኤል  በንግግራቸው  የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆን በወንጀልና በፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ዘርፍ የሚፈፀሙ ተግባራት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፣ በተለይም ቅጣቶች በፍትሃዊነት፣ በወጥነትና በሕግ መሠረት እንዲወሰኑ የተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ 3/2017 ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
በሥልጠናው ወቅት ዐቃቢያነ ህግ በወንጀል ቅጣት አወሳሰን ሂደት ተገቢ የቅጣት አስተያየት በመስጠት የፍትህ ሥርዓቱን ወጥነትና ተዓማኒነት በማስጠበቅ ያላቸው ሚና በስፋት ተዳሷል።
በተጨማሪም በፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ዘርፍ የመንግስትና የሕዝብ ጥቅም እንዲጠበቅ፣ የግዥ ውሎችና ሌሎች የመንግስት ጉዳዮች በሕግ መሠረት እንዲፈፀሙ እንዲሁም ከህገ-ወጥ ተግባራትና ከኪሳራ ለመከላከል የዐቃቢያነ ህግ ሚና ወሳኝ መሆኑ ተጠቅሷል።
በመድረኩ ላይ በወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 ላይ ያተኮረ የመወያያ ሰነድ በክልሉ ዐቃቤ ሕግ በአቶ ደጀኔ ማቲዎስ የቀረበ ሲሆን፣ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍትሕ አስተዳደር የዐቃቤ ሕግ ሚናን የተመለከተ ጽሑፍ ደግሞ በዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ በአቶ አሊ ሰይድ አማካኝነት ቀርቧል።
ሥልጠናው የሙያ ብቃትን ለማሳደግ፣ ወጥ አሰራርን ለማጠናከር እና የፍትህ አገልግሎትን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው  ተገልጿል።
ተሳታፊዎችም በሥልጠናው የሚቀርቡ ሐሳቦችን በጥልቀት በመከታተልና ልምድ በመጋራት የተሻለ የፍትህ አገልግሎት ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

Image
የቅጣት አወሳሰን መመሪያ 3/2017 እና የፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ዙሪያ የዐቃቢያነ ህግ አቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተካሄደ