Skip to main content

የሥራ ሥነ-ምግባር ግንባታ ለተቋማት ውጤታማነትና ለተገልጋይ እርካታ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
ሀላባ፣ ሰኔ 2/2018 ዓ.ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፍትህ ቢሮ የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ለቢሮው አመራሮችና ሠራተኞች በሥራ ሥነ-ምግባር ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና ሰጠ።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የቢሮው ምክትል ኃላፊና የህግ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም በድሩ፣ የሥራ ሥነ-ምግባር በታታሪነት፣ በተጠያቂነትና በቁርጠኝነት ሥራን በመከወን የሚረዳ መሠረታዊ እሴት መሆኑን ገልፀው፣ ተቋማት ተልዕኳቸውን በተሳካ ሁኔታ ለማሳካት የሚያስችላቸው ዋና መሠረት መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ አብርሃም አክለውም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የተገልጋዮች ፍላጎት  ለማሟላት ሠራተኞች ከፍተኛ የሥራ ሥነ-ምግባር ሊላበሱ እንደሚገባ ገልፀዋል። ጥሩ የሥራ ሥነ-ምግባር ያላቸው ሠራተኞች ለከፍተኛ ኃላፊነትና ለሥራ ዕድገት እንደሚመረጡ ሲገልጹ፣ የሥራ ሥነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸው ሠራተኞች የተቋማትን ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት እንቅፋት እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።
በስልጠናው ላይ የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የስነ-ምግባር አውታሮች ማስተባበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱልሽኩር ቡሴር በሥራ ሥነ-ምግባር፣ በተጠያቂነት፣ በሙያዊ ታማኝነት፣  እና በተገልጋይ ተኮር አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ዝርዝር ገለፃ አቅርበዋል።
በስልጠናው ወቅት ተቋማት ውጤታማና ትርፋማ ለመሆን የሰው ሀብታቸውን በዕውቀትና በክህሎት ብቻ ሳይሆን በጠንካራ የሥራ ሥነ-ምግባር ማነጽ እንደሚገባቸው ተገልጿል። በተጨማሪም ኢ-ሥነ-ምግባራዊ ድርጊቶችና ሙስና በተቋማት ውስጥ የውጤታማነትና የተገልጋይ እርካታ መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸው ተጠቁሟል።
በውይይቱ ወቅት ተሳታፊዎች የሥራ ሥነ-ምግባር በተቋማት ውስጥ ጠንካራ የአገልግሎት ባህል ለመፍጠር፣ የተገልጋዮችን እምነት ለማጠናከርና የሥራ ውጤታማነትን ለማሳደግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። ስልጠናው በየዕለቱ በሥራ ቦታ የሚያጋጥሙ የሥነ-ምግባር ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ጠቃሚ ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸውም ገልፀዋል።
በተለይም ተሳታፊዎቹ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በተግባር በመተርጎም ተገልጋይ ተኮር፣ ተጠያቂና ግልጽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
ስልጠናው በተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት የታጀበ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ተጠናቋል።

Image
የሥራ ሥነ-ምግባር ግንባታ ለተቋማት ውጤታማነትና ለተገልጋይ እርካታ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ