Skip to main content

የዐቃቤ ህግ አስተዳደርን እና ሙያዊ አፈጻጸምን ለማጠናከር የተዘጋጁ አራት ረቂቅ መመሪያዎች በማኔጅመንት ውይይት ግብዓት ተሰበሰበ******

ሀላባ፣ ሰኔ 24/2018 ዓ.ም. የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የዐቃቤ ህግ ተቋማዊ አስተዳደርን፣ ሙያዊ ሥነ-ምግባርንና የሥራ አፈጻጸምን የበለጠ ቀልጣፋ፣ ግልጽ እና ውጤታማ ለማድረግ ያለሙ አራት ረቂቅ መመሪያዎችን ለማፅደቅ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ከቢሮው ኃላፊዎችና ከማኔጅመንት አባላት ጋር ለሁለት ቀናት የቆየ ዝርዝር ውይይት አካሂዷል።

በሰኔ 23 እና 24/2018 ዓ.ም. በሀላባ በተካሄደው የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ፣ የዐቃቤ ህግ ሥነ-ምግባር አፈጻጸም፣ የቅጥር፣ የምደባና የዝውውር አፈጻጸም፣ የዐቃቤ ህግ አስተዳደር ጉባኤ አባላት የስብሰባ ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም የዐቃቤ ህግ የሥራ አፈጻጸም ምዘናን የሚመለከቱ አራት ረቂቅ መመሪያዎች በዝርዝር ቀርበው ተመርምረዋል።

ረቂቅ መመሪያዎቹ አንቀጽ በአንቀጽ ከቀረቡ በኋላ የማኔጅመንት አባላት የመመሪያዎቹ ይዘት፣ ቅርጽና ተግባራዊነት የበለጠ እንዲጠናከር የሚያግዙ ገንቢ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን አቅርበዋል። በቀረቡት ሀሳቦች ላይም የረቂቅ አዘጋጅ ቡድኑ ዝርዝር ማብራሪያ በመስጠት ውይይቱን የበለጠ ፍሬያማ አድርጎታል።
በመድረኩ የተሰበሰቡ ግብዓቶች እና ማሻሻያ ሀሳቦች በረቂቅ መመሪያዎቹ ውስጥ ተካተው የመጨረሻ ማስተካከያ እንዲደረግባቸውና ለፀደቃ ጉባኤ በሚቀርብ ደረጃ እንዲዘጋጁ የቢሮው ማኔጅመንት አቅጣጫ አስቀምጧል።

የፍትህ ቢሮው እነዚህ መመሪያዎች ሲፀድቁ በዐቃቤ ህግ አገልግሎት ውስጥ የሙያ ሥነ-ምግባርን፣ የሰው ኃይል አስተዳደርን፣ የአፈጻጸም ምዘናን እና ተቋማዊ አስተዳደርን በማጠናከር የፍትህ አገልግሎቱን ጥራትና ተጠያቂነት የበለጠ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም በቀጣይ የሚዘጋጁ እና የሚፀድቁ ሌሎች መመሪያዎችም ተመሳሳይ ተሳትፎና ግብዓትን ማዕከል በማድረግ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
 

Image
የዐቃቤ ህግ አስተዳደርን እና ሙያዊ አፈጻጸምን ለማጠናከር የተዘጋጁ አራት ረቂቅ መመሪያዎች በማኔጅመንት ውይይት ግብዓት ተሰበሰበ