የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋና ምቹ በማድረግ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት እየተሰራ ነው - የክልሉ ፍትህ ቢሮ
ሀላባ፣ ነሀሴ 30/2018 ዓ.ም) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሴክተር ጉባኤውን ከባለድርሻ አካላት ጋር በሀላባ ቁሊቶ ከተማ አካሂዷል።
የቢሮው ሀላፊ አቶ አክመል አህመዲን እንደተናገሩት የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋና ምቹ በማድረግ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ዐቃቤ ህግ ከቀረቡለት መዝገቦች መካከል 98 በመቶ ላይ ውሳኔ መሰጠት መቻሉን የተናገሩት አቶ አክመል የመርታት ምጣኔውንም 97 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
መጠነ ማቋረጥንም በባለፈው በጀት ዓመት ከነበረበት 467 መዝገብ ወደ 366 ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረው አሁንም ተጨማሪ ሰፊ ስራ የሚጠይቅ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።
ጉባኤው በበጀት ዓመቱ አመርቂ ውጤት የተመዘገበባቸውን ተግባራት አጠናክሮ ለማስቀጠልና ዝቅተኛ አፈጻጸም የተመዘገበባቸውን ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለመፈጸም አቅም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ መነቴ ሙንዲኖ እንደተናገሩት በክልሉ ፍትህ በእኩልነት የሚደርስበት ማህበረሰብን ለመፍጠር ሁላችንም ሀላፊነታችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
ለህግ የበላይነትና ዘላቂ ፍትህ መስፈን ተቋማዊ ቅንጅትን ማሳደግ ይገባል ያሉት ወይዘሮ መነቴ የፖሊስና የማረሚያ ቤቶች ማረፊያ ቦታዎች የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ያከበረ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል የወንጀል እና ፍትሃብሄር ዘርፍ አቶ እያሱ ሻንቆ በበኩላቸው የፍትህ ስርዓት መዘግየትና ሌሎች የፍትህ ስርዓት የሚያደናቅፉ ችግሮችን ማስወገድ የጋራ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።
የሀገራችን የብልጽግና ጉዞ በብልሹ አሰራር እንዳይደናቀፍ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማክበር ትኩረት የሚሻው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በአገልግሎት አሰጣጡ የሚነሱ የዜጎች የአገልግሎት እሮሮ ለመቀነስ የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች ብልሹ አሰራር በማስወገድ የተገልጋዩችን እርካታ ከፍ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለዜጎች ተገቢውን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በተደጋጋሚ በየአካባቢው በፌትህ ስርዓቱ ላይ የሚነሱ የህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መቅረፍ ይገባል ብለዋል።
በምርመራ ሂደት ያለውን የወጥነት ችግር መቅረፍ፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እና ባህላዊ ዳኝነትን በማስፋት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ቢሮው የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ዞኖች እና ልዩ ወረዳ የእውቅናና ሰርተፍኬት ሽልማት አበርክቷል።