የዐቃቤ ሕግን ተቋማዊ አስተዳደርና ሙያዊ አፈጻጸም የሚያጠናክሩ አራት መመሪያዎች በዋና ጉባኤ ጸደቁ
ሀላባ፣ ጥቅምት 24/2019 ዓ/ም
የዐቃቤ ሕግን ተቋማዊ አስተዳደር፣ ሙያዊ ሥነ-ምግባርና የሥራ አፈጻጸም የበለጠ ግልጽ፣ ፍትሐዊና ውጤታማ ለማድረግ የተዘጋጁ አራት መመሪያዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የዐቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ጸደቁ።
በሀላባ በተካሄደው የዋና ጉባኤው ስብሰባ የጉባኤው ሰብሳቢና የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻን ጨምሮ የጉባኤው አባላት ተሳትፈዋል።
በጉባኤው የጸደቁት መመሪያዎች የዐቃቤ ሕግ ሥነ-ምግባር አፈጻጸም መመሪያ፣ የቅጥር፣ የምደባና የዝውውር አፈጻጸም መመሪያ፣ የዐቃቤ ሕግ አስተዳደር ጉባኤ አባላት የስብሰባ ሥነ-ሥርዓት መመሪያ እንዲሁም የዐቃቤ ሕግ የሥራ አፈጻጸም ምዘናን መመሪያ የሚመለከቱ ናቸው።
መመሪያዎቹ ከመጽደቃቸው በፊት በቢሮው ማኔጅመንት አባላት፣በ 0ቃቢያነ ህግ ባለሙያዎች፣ በቢሮው ከፍተኛ አመራሮች የተለያዩ ውይይቶችና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች የተካሄዱ ሲሆን፣ የተሰበሰቡ ማሻሻያ ሀሳቦችና ግብዓቶች ተካተው ለዋና ጉባኤው ቀርበዋል።
በጉባኤው ውይይት ወቅት የቅጥር፣ የምደባና የዝውውር ሂደቶች በግልጽ መስፈርትና በፍትሐዊነት እንዲፈጸሙ፣ የሰው ኃይል አስተዳደርም በሕግና በመመሪያ አግባብ እንዲመራ አስፈላጊነቱ ተነስቷል። በተጨማሪም የዐቃቤ ሕጎች ሙያዊ ሥነ-ምግባርን፣ የአለባበስ ሥርዓትንና የተቋሙን ክብር የሚጠብቅ ባህሪ ማጠናከር፣ የአስተዳደር ጉባኤውም በተቀመጠላት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በመሰብሰብ የተቋሙን አሠራር መከታተል እንዳለበት ሀሳቦች ቀርበዋል።
እንዲሁም የሥራ አፈጻጸም ምዘናው በወጥ መስፈርት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲተገበር፣ የባለሙያዎች የሥራ ውጤትና ብቃት በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲመዘንና የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንዲጠናከር አስፈላጊነቱ ተገልጿል።
በአጠቃላይ የጉባኤው አባላት መመሪያዎቹ በጥናትና በዝርዝር ውይይት መዘጋጀታቸውን በማድነቅ፣ የተነሱት ማሻሻያ ሀሳቦች በመመሪያዎቹ ውስጥ መካተታቸውን ተከትሎ በጉባዔው ፀድቀዋል።
አራቱ መመሪያዎች መጽደቃቸው በዐቃቤ ሕግ ተቋም የሙያ ሥነ-ምግባርን፣ የሰው ኃይል አስተዳደርን፣ የሥራ አፈጻጸም ምዘናንና ተቋማዊ ተጠያቂነትን በማጠናከር የፍትህ አገልግሎቱን ጥራትና ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑ ተጠቁሟል።
ፍቅርተ ዘለቀ
የቢሮው መ/ኮሚኒኬሽን